ዩክሬን በ2024 መጨረሻ በምታዘጋጀው የሰላም ጉባኤ ላይ ሩስያ እንድትሳተፍ እንደምትፈልግ አስታወቀች
በሰላም ጉባኤው ላይ ከሩስያ ጋር ቀጥተኛ የሁለትዮሽ ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት ግን ገልጻለች
ሞስኮ በዩክሬን የተሳትፎ ጥሪ ዙርያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም
ዩክሬን በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መጠናቀቂያ ላይ በምታዘጋጀው የሠላም ጉባኤ ላይ የሩስያ ልኡካን እንዲሳተፉ እንደምትፈልግ ገልጻለች፡፡
ከዚህ ቀደም ባዘጋጀቻቸው የተለያዩ የአለም ሀገራት መሪዎች በታደሙበት የሰላም ጉባኤዎች ላይ የሩስያን መሳተፍ አጥብቃ ስትቃወም የነበረችው ዩክሬን ለመጀመርያ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ለማሳተፍ ፈቃደኛ ሆናለች፡፡
ሞስኮ ያልተሳተፈችበት የሰላም ምክክር የተጓደለ ነው በሚል ሲተች የነበረው የዘለንስኪ አስተዳደር ከሀገሪቷ ጋር ፊት ለፊት የሁለትዮሽ ውይይት የማድረግ እቅድ ባይኖረውም በጉባኤው ላይ ግን ትሳተፍ ዘንድ ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡
ጦርነቱ ሶስት አመቱን ሊደፍን ሲቃረብ ሁለቱ ሀገራት በጥቁር ባህር በኩል የእህል ምርቶች እንዲተላለፉ ከተነጋገሩበት መድረክ በስተቀር ፊት ለፊት ስለ ሰላምም ሆነ ስለተኩስ ማቆም ተወያይተው አያውቁም፡፡
ቱርክ ፣ ቻይና እና ብራዚል ሁለቱን ሀገራት ለማደራደር እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማስማማት ፈቃደኛ መሆናቸውን ቢያሳውቁም ከተዋጊዎቹ ወገን ይሁንታ አላገኙም፡፡
በአለም አቀፍ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው የሚነገርለት የምዕራቡ አለም ደግሞ በይፋ ውግንናውን ለዩክሬን በመግለጽ በቢሊየን ዶላር ግምት ያላቸው የጦር መሳርያዎችን እያስታጠቀ ነው፡፡
በዚህ መካከል ጦርነቱ የሚቆምበት ጊዜ ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ ተራዝሞ መቀጠሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በቅርቡ ከዋነኛ አጋራቸው ዋሽንግተን ዘንድ የነበሩት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪ በሩስያ ላይ ተጨማሪ ሁለንተናዊ ጫናዎች እንዲበረቱ የሚጠይቀውን “የድል እቅድ” ያሉትን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ዩክሬን ሩስያ በተቆጣጠረቻቸው እና ህዝበ ውሳኔ ያስደረግችባቸውን ስፍራዎች እውቅና ስትሰጥ እንዲሁም የኔቶ አባል ለመሆን ያቀረበችውን ሀሳብ ስትሰርዝ ስለ ሰላም መነጋገር እንችላለን በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል፡፡
በቱርክ የዩክሬን አምባሳደር በ2024 መጨረሻ ይደረጋል የተባለውን ሀገራቸው የምታዘጋጀውን የሰላም ጉባኤ አስመልከተው ባደረጉት ንግግር “እያወራን ያለነው በጉባኤው ላይ የዩክሬን እና ሩስያ ልዑካን ፊት ለፊት ተቀምጠው ስለፍላጎቶቻቸው ስለሚያወሩበት መድረክ አይደለም፤ ይልቁንስ በዩክሬን እንዴት ሰላም ማስፈን እንደሚቻል የሚመከርበት ነው” ብለዋል፡፡
በሰላም ጉባኤው በኪቭ ሰማይ ሰር ሰላምን ለመመለስ መወሰድ ስለሚኖርባቸው እርምጃዎች ከአለምአቀፉ ማሕበረሰብ ጋር እንወያያለን ያሉት አምባሳደሩ የሩስያ ልኡክ በቦታው መኖር አቋማችንን ፊት ለፊት ለመግለጽ የሚያግዘን ይሆናል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኪቭ ባሰናዳቻቸው የሰላም ጉባኤዎች ላይ ባለመሳተፏ ጉባኤው “የይስሙላ” እንደሆነ ስታጣጥል የነበረችው ሞስኮ ዩክሬን ባቀረበችው የተሳትፎ ጥሪ ዙርያ እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልሰጠችም፡፡