የሩሲያ ኃይሎች ሌላኛዋን ቁልፍ የዩክሬን ከተማ ለመቆጣጠር ተቃረቡ
የሩሲያ ኃይሎች ቩሌዳር ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቶሬስክ ከተማ ዳርቻ መድረሳቸውን የዩክሬን ጦር በትናንትናው እለት ገልጿል
ሩሲያ በጋይድድ ቦምቦች ታግዛ እያንዳንዱን መንደር በመቆጣጠር ከባለፈው ነሐሴ ጀምሮ ወደ ቶሬስክ ስትገሰግስ ቆይታለች
የሩሲያ ኃይሎች ሌላኛዋን ቁልፍ የዩክሬን ከተማ ለመቆጣጠር ተቃረቡ።
የሩሲያ ኃይሎች ወሳኝ የተባለችውን በከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኘውን ቩሌዳር ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በምስራቅ ዩክሬኗ የግንባር ከተማ ቶሬስክ ዳርቻ መድረሳቸውን የዩክሬን ጦር በትናንትናው እለት ገልጿል።
"ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም፤ በከተማዋ በሁሉም መግቢያዎች ውጊያ እየተካሄደ ነው"ሲል የሉሀንስክ ዘመቻ ቃል አቀባይ አናስታሲያ ቦቮኒኮቫ ለዩክሬን ብሔራዊ ቴሌቪዥን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"የሩሲያ ኃይሎች በከተማዋ ምስራቃዊ ዳርቻ ገብተዋል።"
በትናንትናው እለት በቶሬስክ አቅራቢያ ጨምሮ በበርካታ መንደሮች በዩክሬን ጦር የሰው ኃይል እና መሳሪያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የገለጸው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስተያየት አልሰጠም።
ታዋቂውን የራይባር ቴልግራም ቻናል የሚመሩትን ወታደራዊ ተንታኞች ጨምሮ የሩሲያ ወታደራዊ ጸኃፊዎች የሩሲያ ኃይሎች ወደ ከተማዋ መሀል እየገፉ ናቸው ብለዋል። የሩሲያ ኃይሎች ቩሌዳርን ከተቆጣጠሩ በኋላ እያደረጉት ያለው ግስጋሴ ያላቸውን የጦር መሳሪያ እና የሰው ኃይል ብልጫ ያሳየ ነው ተብሏል።
1/5 የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት የተቆጣጠረችው ሩሲያ ከፍተኛ ውድመት በሚያስከትሉት ጋይድድ ቦምቦች ታግዛ እያንዳንዱን መንደር በመቆጣጠር ከባለፈው ነሐሴ ጀምሮ ወደ ቶሬስክ ስትገሰግስ ቆይታለች።
አሁን ላይ ዩክሬን በርካታ ግዛቶችን እያጣች ሲሆን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሞስኮ በግንባር ያላትን ግስጋሴ ለመቀነስ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ለከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ቶሪስክ በ2014 በሩሲያ በሚደገፉ ተገንጣዮች የተያዙትን ቦታዎች ስለምታዋስን ለዩክሬን ለ10 አመታት ያህል የግንባር ከተማ ሆናለች። ከእዚያ ጊዜ ወዲህ ከተማዋ የኪቭ ምሽግ ነች።
ለሞስኮ ደግሞ የከተማ መያዝ የፕሬዝደንት ፑቲን ዶምባስን የመቆጣጠር እቅዳቸው ለመሳካት እንዲቃረብ ያደርጋል።
የዩክሬን ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ኮረብታ ጫፍ ያለችው ከተማ መያዝ ሞስኮ የፖክሮቭስክ-ኮስትያንቲኒካ መስመርን ጨምሮ የኪቭ ኃይሎችን የሎጂስቲክ እንቅስቃሴ መስመር እንድትዘጋ ያስችላታል።
ሞስኮ በየካቲት 2022 ባደረገችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭን ለመያዝ ያደረገችው ጥረት ከከሸፈ በኋላ ፕሬዝደንት ፑቲን ትኩረታቸውን በምስራቅ ዩክሬን ያለውን ሉሀንስክ እና ዶኔስክ ግዛቶችን በሚያጠቃልለው ዶምባስ ላይ አድርገዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ቅደመ ሁኔታዎች የተራራቁ በመሆናቸው ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ፍሬ አላፈሩም።
ዩክሬን ጦርነቱ እንዲቆም የሩሲያ ኃይሎችን ከግዛቷ ሙሉ በሙሉ መውጣት በቅደመ ሁኔታነት ስታስቀምጥ፣ ሩሲያ ደግሞ ዩክሬን በአራቱ ግዛቶች ላይ ያላትን ጥያቄ እንድትተው ጠይቃለች።