ሚንስትሩ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ያቋረጡት ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ አዲስ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ነው
የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር የአፍሪካ ጉብኝታቸው አቋረጡ።
የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድሚትሮ ኩሌባ አፍሪካን ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በመጎብኘት ላይ ናቸው።
ሚንስትሩ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሆነችው ሴኔጋል የጀመሩ ሲሆን ከፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር ውይይት አድርገዋል።
በመቀጠልም ኩሌባ ጉብኝታቸውን ወደ ኮቲዲቯር አድርገው ከሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋልም ተብሏል።
ከትናንት በስቲያ ክሪሚያን ከተቀረው ሩሲያ ጋር የሚያስተሳስረው ድልድይ በዩክሬን እንደተመታባት የገለጸችው ሩሲያ የዩክሬን ዋና ዋና ከተሞችን በሚሳኤል መደብደቧን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ ሚሳኤል በተለይም የዩክሬን ዋና ከተማ የሆነችው ኪቭን ደጋግሞ መምታቱን ተከትሎ በከተማዋ ውጥረት የነገሰ ሲሆን ባቡርን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ተብሏል።
የዩክሬን- አፍሪካ ጉባኤ እንዲካሄድ እና አፍሪካዊያን ሩሲያን እንዲያወግዙ ለማድረግ ወደ አፍሪካ የመጡት የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድሚትሮ ኩሌባም ጉብኝታቸውን እንዳቋረጡ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ሚንስትሩ በአፍሪካ የጀመሩትን ጉብኝት ያቋረጡት ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ አዲስ ጥቃት በመሰንዘሯ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ ሰባት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
የጀርመን መንግስት ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ሪፖርት ከሆነ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዩክሬናዊያን በሀገሯ አስጠልላለች።
ሩሲያ ከሁለት ሳምንት በፊት ከዚህ በፊት የዩክሬን ግዛት የነበሩ አራት ግዛቶችን በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ጠቅልላለች።