በክሬሚያ በድልድይ ላይ ከደረሰ ፍንዳታ ጀርባ የዩክሬን እጅ እንዳለ ሩሲያ አስታውቃለች
የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን በሽብርተኝነት ከሰሱ፡፡
ፑቲን ዩክሬንን በሽብርተኝነት የከሰሱት በአውሮፓ ረዥሙና (12 ማይል) ከሩሲያ ወደ ክሬሚያ የሚወስደው ብቸኛ ድልድይ ከደረሰው ፍንዳታ ጀርባ እጇ አለ በሚል ነው፡፡
ለሩሲያ ጠቃሚ ስትራቴጂካዊ እና ተምሳሌታዊ እሴት እንዳለው በሚነገርለት ድልድይ ላይ ቅዳሜ እለት በደረሰው ፍንዳታ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን መርማሪዎች ተናግረዋል።
በፍንዳታው ድልድይ ላይ ያለው የመንገድ እና የባቡር ትራፊክ ከመቆሙ በተጨማሪ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ያሉት የሩሲያ ጦር ኃይሎች አስፈላጊው እቅርቦት እንዳያገኙ ምክንያት ሆኗል እየተባለ ነው፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት በድልድዩ ላይ ለደረሰው ውድመት ዩክሬንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ፑቲን “ምንም ጥርጥር የለም፤ ይህ ወሳኝ የሆኑ የሲቪል መሰረተ ልማቶችን ለማጥፋት ያለመ የሽብር ተግባር ነው" ሲሉ እሁድ ዕለት በክሬምሊን የቴሌግራም ቻናል ላይ በተለጠፈው ቪዲዮ ላይ ተናግረዋል።
ይህ ሆን ተብሎ በትእዛዝ የተከናወነ ነውም ማለታቸውንም የኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንትና የሀገሪቱ የደህንነት ም/ቤት ምክትል ኃለፊ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ሩሲያ "አሸባሪዎችን" መግደል አለባት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“ሩሲያ ለዚህ ወንጀል ምላሽ መስጠት የምትችለው አሸባሪዎችን በቀጥታ በመግደል ብቻ ነው፣ በሌላው ዓለም እንደተለመደው፤ ይህ የሩሲያ ዜጎች የሚጠብቁት ነው " ሲሉም ነው የተናገሩት ሜድቬዴቭ፡፡
በ2018 የተከፈተውና ከባድ ፍብዳታ የደረሰበት ድልድይ እና የባቡር ሃዲድ ሩሲያ አሁን ላይ ለዩክሬን ጦርነት የምትጠቀምበትን ሎጂስቲክ የምታገኝበት ቁልፍ መስመር ነው።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ አማካሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ የዩክሬን ኃላፊነት በቀጥታ ባይቀበሉም “ክሪሚያ፣ ድልድይ፣ መጀመሪያው” የሚሉ ቃላትን አስፍረዋል።
"ህገ ወጥ ነገር ሁሉ መወገድ አለበት፤የተሰረቀው ነገር ሁሉ ወደ ዩክሬን መመለስ አለበት፤ በሩሲያ የተያዘው ነገር ሁሉ መባረር አለበት" ብለዋል።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር የድልድዩን ፍንዳታ በሚያዝያ ወር ከሰጠመችው የሩስያዋ ሞስኮቫ የሚሳኤል መርከብ ጋር አነጻጽሮታል።
"በዩክሬን ክሬሚያ ውስጥ የነበሩ ሁለት ታዋቂ የሩሲያ የታላቅነት ምልክቶች ወድመዋል። በቀጣይስ ምን አለ?" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የዩክሬን መንግስት በትዊተር ገጹ “ተቃጥሏል” የሚል ጽሁፍ አጋርቷል፡፡
የዩክሬን ባለስልጣናት ባህረ ሰላጤውን (የክሬሚያ ግዛትን) መልሰው ለመውሰድ ቃል ስለገቡ ይህ ትክክለኛ ዒላማ ነው ብለዋል ።
ከፍተኛ የሩስያ ጦር ባለባት በክሬሚያ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት ለክሬምሊን ሌላ ትልቅ ውርደት ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።