የጥቁር ባህር እህል ስምምነት መራዘሙን ተመድ አስታወቀ
የዓለምን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ የተደረሰው ስምምት ከዩክሬን ሦስት ወደቦች እህል ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ነው
ሩሲያ በበኩሏ በስምምነቱ ማዳበሪያ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትፈልጋለች ተብሏል
የዩክሬን የግብርና ምርትን ከደቡባዊ ጥቁር ባህር ወደቦች በማመቻቸት የዓለምን የምግብ እጥረት ለማቃለል ያለመው ስምምነት ለአራት ወራት ተራዝሟል።
በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የተደረሰው ስምምነቱ ጥብቅ የባህር መሸጋገሪያን የፈጠረ ሲሆን፤ ዋና ዋና የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች አምራች ከሆነችው ዩክሬን ሦስት ወደቦች ወደ ውጭ መላክ እንዲጀምር ያደረገ ነው።
ስምምነቱ የዓለምን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ የተደረሰም ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሰጡት መግለጫ “ከዩክሬን የሚመጡ እህሎች፣ ምግቦች እና ማዳበሪያዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞን ለማመቻቸት የጥቁር ባህር የእህል ስምምነትን በደስታ እቀበላለሁ” ብለዋል።
ጉቴሬዝ ተመድ “ከሩሲያ ምግብ እና ማዳበሪያን ወደ ውጭ ለመላክ መንገድ ለማመቻቸትም ቁርጠኛ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የጥቁር ባህር እህል ስምምነቱ እ.አ.አ ከህዳር 18 ጀምሮ ለ120 ቀናት መራዘሙን አረጋግጧል።
ለማዳበሪያ ጠቃሚ ንጥረ ነገር ነው የተባለውን አሞኒያን ሩሲያ በቧንቧ ወደ ጥቁር ባህር ለመላክ የታደሰው ስምምነት አካል ቢሆንም እስካሁን ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰበት ውይይቱን የሚያውቁ ሁለት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በመስከረም ወር ላይ ሞስኮ የጦር እስረኞችን ከመለሰች በዩክሬን በኩል የሩስያ አሞኒያ በሀገራቸው በኩል ለመክፈት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረው ነበር ተብሏል።
ስምምነቱ ለ120 ቀናት መራዘም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዩክሬን ከጠየቁት አንድ አመት ያነሰ ነው ተብሏል።
ሩሲያ ቀደም ሲል የጥቁር ባህርን የእህል ስምምነት ለማራዘም ሞስኮ የራሷን እህል እና ማዳበሪያ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተመሰረተ ነው ማለቷን ዘገባው አስታውሷል።
እስካሁን በጥቁር ባህር ስምምነት 11 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርቶችን ጨምሮ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን በቆሎ ወደ ውጭ ተልኳል ነው የተባለው። ከአጠቃላይ የግብርና ምርቶቹ ስንዴ 29 በመቲውን ይይዛል።