በዩክሬን ፕሪሚየር ሊግ “ረጅሙ” ጨዋታ ከ4 ስአት ከ36 ደቂቃ በኋላ ተጠናቋል
በዲኒፕሮ ከተማ የተካሄደው ጨዋታ በአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ምክንያት በተደጋጋሚ ተቋርጧል
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት በእግርኳስ ውድድሮችም ላይ ተጽዕኖውን እያሳረፈ ነው
የዩክሬን ፕሪሚየር ሊግ ትናንት ምሽት በታሪኩ ረጅም ስአት የወሰደውን ጨዋታ አስተናግዷል።
በዲኒፕሮ አሬና የተደረገው የዲኒፕሮ 1 እና ኦሌክሳንድሪያ ጨዋታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ 4 ስአት ከ36 ደቂቃዎች ተቆጥረዋል።
በከተማዋ የሚሳኤል ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ ድምጽ ጨዋታው 15 ደቂቃዎች ዘግይቶ እንዲጀመር አድርጓል።
ዲኒፕሮ በመጀመሪያው አጋማሽ በ34ኛው ደቂቃ መሪ የሆነበትን ጎል ያስቆጠረ ሲሆን፥ ኦሌክሳንድሪያ ከእረፍት መልስ አቻ የሚያደርገውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ይሁን እንጂ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያው በድጋሚ በመሰማቱ ጨዋታው ለ1 ስአት ተቋርጦ ዳግም ወደ ሜዳ ሲመለሱ ጎሊ በቪዲዮ ዳኝነት (ቫር) ታይቶ ተሽሮበታል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረውም ማስጠንቀቂያው በማስተጋባቱ ጨዋታው ለስአታት ተቋርጧል።
ከሁለት ጊዜ በላይ የተራዘመው ጨዋታ የውጤት ለውጥ ሳይኖረው ከ4 ስአታት ከ36 ደቂቃዎች በኋላ ተጠናቋል ነው የተባለው።
አስተናጋጁን ክለብ ዲኒፕሮ 1 በዩክሬን ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን እንዲይዝ ያደረገው ጨዋታ በሊጉ ታሪክ ረጅም ስአት የወሰደ ተብሎ ተመዝግቧል።
ከዚህ ቀደም ክብረወሰን ሆኖ የተመዘገበው ኤፍሲ ሩክ እና ኤፍሲ ሜታሊስት የተባሉት ክለቦች ከ4 ስአት ከ27 ደቂቃዎች በኋላ ያጠናቀቁት ጨዋታ እንደነበርም የዩክሬን ፕሪሚየር ሊግ አስታውቋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከሚፋለሙበት የጦር ቀጠና ርቃ በምትገኘው ዲኒፕሮ ከተማ ከትናንት በስቲያ አንድ አዛውንት በሞስኮ የአየር ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ በትናንቱ ጨዋታ ላይ ከፍ ያለ ስጋት ፈጥሮ ነበር።
የዲኒፕሮ ክለብ ተከላካዩ ኤድዋርድ ሳራፒ ረጅም ጊዜ የወሰደው ጨዋታ በክለቡ አሸናፊነት ቢደመደምም በተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አልሸሸገም።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የዩክሬን ፕሪሚየር ሊግ አሁንም ከፍተኛ ስጋት እንደተደቀነበት የትናንቱ የዲኒፕሮ እና ኦሌክሳንድሪያ ጨዋታ ማሳያ ሆኗል።