የዩክሬን እና ሞልዶቫ መግባት የአውሮፖ ህብረትን አለመረጋጋት ውስጥ ይከተዋል-ሩሲያ
ህብረቱ ከዩክሬን በተጨማሪ የሶቬት ህብረት አባል የነበረችውን ጆርጂያን እጭ አባል አድርጓታል
ህብረቱ ከሀንጋሪ ባጋጠመው ተቃውሞ ምክንያት ለዩክሬን ሊሰጥ በነበረው 50 ቢሊዮን ዩሮ ላይ ሳይስማማ ቀርቷል
ዩክሬን እና ሞልዶቫ ወደ አውሮፖ ህብረት የሚገቡ ከሆነ ህብረቱ ወደ አለመረጋጋት ውስጥ ይገባል ስትል ሩሲያ አስጠንቅቃለች።
ህብረቱ የዩክሬን እና ሞልዶቫ የአባልነት ጥያቄ ለውይይት ክፍት እንዲሆን በማድረግ የፖለቲካ ውሳኔ መወሰኑን የተናገረችው ሩሲያ ጉዳዩን የተቃወመችውን ሀንጋሪን አድንቃለች።
የሩሲያ ቤተመንግስት ወይም ክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮፕ "ወደ ህብረቱ ለመግባት የሚደረገው ድርድር አመታትን ይፈጃል። አውሮፖ ህብረት ያለውን ጥብቅ መስፈርት ዩክሬንም ሆነች ሞልዶቫ አያሟሉትም" ብለዋል።
ዩክሬን፣ ሩሲያ አላማዋ እስከሚሳካ እንደምትቆይ በገለጸችው ጦርነት ውስጥ ብትሆንም፣ የህብረቱ መሪዎች በትናንትናው እለት ባደረጉት ስብሰባ የዩክሬን የአባልነት ጥያቄ ለውይይት ክፍት እንዲሆን ተስማምተዋል።
ይህን የህብረቱን እርምጃ የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን ተቃውመውታል።
ህብረቱ ከዩክሬን በተጨማሪ የሶቬት ህብረት አባል የነበረችውን ጆርጂያን እጭ አባል አድርጓታል።
ፔስኮቭ ይህንን ወሳኔም በተመሳሳይ የፖለቲካ ውሳኔ ነው ብለውታል።
ህብረቱ ከሀንጋሪ ባጋጠመው ተቃውሞ ምክንያት ለዩክሬን ሊሰጥ በነበረው 50 ቢሊዮን ዩሮ ላይ ሳይስማማ ቀርቷል።
ፔስኮቭ "ሀንጋሪ የራሷ ፍላጎት አላት። ሀንጋሪ ከሌሎቹ የአውሮፖ ሀገራት በተለየ ሁኔታ ለፍላጎቷ ትቆማለች፤ ይህ አስገርሞናል" ሲሉ ተናግረዋል።