ማክሮን ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በትናንትው እለት በኢትዮያ የአንድ ቀን ይፋዊ የስራ ጉባኝት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አዲስ አበባ ሲደርሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በመሆን እድሳት የተደረገለትን የብሄራዊ ቤተ መንግስት የጎበኙ ሲሆን፤ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ምክክር አድርገዋል።
በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እድሳት የተደረገለት ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አሁን የደረሰበትን ውብ ገፅታ እንዲላበስ ትልቁን ድርሻ ለሚወስዱት ፕሬዝዳንት ማክሮን ምስጋና አቅርበዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ለማደስ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰው፤ እድሳቱ ከግማሽ በላይ መጠናቀቁን እና በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ፈረንሣይና ቻይና ተባባሪ ሊቀ-መናብርት ሆነው በሚመሩት የፓሪስ ክለብ ፕሬዝዳንት ማክሮን ላቅ ያለ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።
ማክሮን በኤክስ ገጻቸው በአማርኛ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ሀገራቸው ፈረንሳይ "የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዘመንን ተግባዊ ለማድረግ ትብብር እንደምታርግ ገልፀዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ማክሮን ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እያደረገች ስላለው ጥረት በዝርዝር መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብና ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለች ሀገር እንደመሆኗ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ሁለቱ መሪዎች መነጋራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደነቁት ፐሬዝዳንት ማክሮን፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ዙሪያም በመምከር በጋራ ለመስራትም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያና ፈረንሣይ ለ127 ዓመት የዘለቀው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለትውልድ እንዲሻገር ሀገራቱ አበክረው እንደሚሰሩ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳት ማክሮን፤ በተለይ የፈረንሣይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኔትዎርክ መስክ እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ ከአውሮፓ ባንኮች የ80 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።
ፈረንሣይ በጤና እና በግብርና መስክ ለኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደመትቀጥልም ፕሬዚደንቱ አረጋግጠዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮያ ይፋዊ የስራ ጉብኝ ሲያደርጉ በስድስት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።