ሩሲያ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ ጀርመኖችን ያሸነፈችበትን የድል ቀን በዛሬው እለት ታከበራለች
ሩሲያ እንደ ናዚ መሸነፏ አይቀርም- ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ
ፕሬዝዳንቱ “የጋራ ጠላቶቻችን (ናዚዎችን) በአንድነት አሸንፈናል፤ ሩሲያም ተመሳሳይ ሽንፈት ይገጥማታል” ነው ያሉት
ሩሲያ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ ጀርመኖችን ያሸነፈችበትን የድል ቀን በዛሬው እለት ታከበራለች
የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ምድር የናዚ ጀርመን ሽንፈትን ይደግሙታል ብለዋል የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ በፈረንጆቹ 1945 ናዚዎችን ያሸነፈችበትን የድል ቀን ከማክበሯ አንድ ቀን በፊት ነው ይህን ያሉት።
“ጥንትም ጠላቶቻችን በአንድነት አሸንፈናል፤ አሁንም ተመሳሳይ ጠላታችን እያፈራረስን ነው” ሲሉም ሩሲያ እንደ ናዚ ጀርመን ሁሉ በዩክሬን ምድር ሽንፈትን እንደምትከናነብ ተናግረዋል።
ጀርመን በፈረንጆቹ ግንቦት 8 1945 ለአሜሪካ፣ ብሪታንያ እና ሶቪየት ህብረት ጥምር ሃይል (አላይድ ፎርስ) እጅ መስጠቷን ተከትሎ ሁለተኛው የአለም ጦርነት መቋጫ እንዳገኘ ይታወሳል።
ሩሲያ እና የቀድሞው የሶቪየት ህብረት አባል ሀገራት ግንቦት 9 የአውሮፓ የድል ቀን አድርገው ያከብሩታል።
ዩክሬንም በተመሳሳይ በዚሁ እለት ድሉን ስታከብር ቆይታለች። ይሁን እንጂ ከሩሲያ ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት ከሞስኮ ጋር የምትጋራቸውን ጉዳዮች እየለወጠች የምትገኘው ኬቭ የድል ቀኑ ግንቦት 8 ላይ እንዲከበር የሚጠይቅ ህግ ለፓርላማዋ አቅርባለች።
ውሳኔውን ያደነቁት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኡርሱላ ቮን ደርላይን ነገ ኬቭ እንደሚገቡና በዚሁ ጉዳይ ላይም እንደሚወያዩ ፍራንስ24 ዘግቧል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አስተያየት የተሰማው ኬቭ 35 የሩሲያ ድሮኖችን መትታ መጣሏን ባሳወቀች በስአታት ልዩነት ነው።
በመዲናዋ ብቻ ከአራት በላይ ንጿሃንን የገደሉትና በርካቶችን ያቆሰሉት የሚሳኤል ጥቃቶች በሌሎች ከተሞችም ህንጻዎችን ስለማፈራረሳቸው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ሞስኮ በናዚዎች ላይ የተቀዳጀችው ድል በዓል ዋዜማ ላይ በዩክሬን ምድር የምትፈጽመው ጥቃት ተጠናክሮ መቀጠሉ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ እየተነገረ ነው።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ግን ዩክሬናውያንን የሚያበረታታ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል ነው የተባለው።
በዩክሬን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ከፍቻለሁ የምትለው ሞስኮ፥ ከኬቭ በኩል የሚነሳውን ወቀሳና ጦርነቱን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ጋር የማያያዝ ሙከራ በተደጋጋሚ ስትቃወም ይደመጣል።
እንደውም ዘመቻው ዩክሬንን “ከናዚያዊ እሳቤ” የማላቀቅ አላማ እንዳለው ማስታወቋ የሚታወስ ነው።