ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከሞስኮ ጥቃት ጋር የዩክሬን ስም መነሳቱ እንዳበሳጫቸው ገለጹ
የሞስኮ የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፉ 4 ተጠርጣሪዎች ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ሲሉ ተይዘዋል ተብሏል
ፑቲን፤ “ሩሲያ በዚህ የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፉና ያገዙ ሁሉንም አካላት ለይታ ትቀጣለች” ሲሉ ዝተዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ባሳለፍነው አርብ በሞስኮ ከተፈጸመው የሽብር ጥቃት ጋር ተያይዞ የሀገራቸው ስም መነሳቱ እንዳበሳጫቸው አስታወቁ።
ባሳለፍነው አርብ በሩሲያዋ ሞስኮ ሲካሄድ በነበረ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 137 መድረሱን እና 100 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው የሩሲያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
በርካታ የሩሲያ ባለስልጣንት ጥቃት እንደተፈጸመ በደቂቃዎች ውስጥ ከጥቃቱ ጀርባ ዩክሬን እንዳለች በመግለጽ፤ ኪቭን ተጠያቂ ሲያደርጉ ተደምጠዋል።
- ፑቲን የሞስኮውን ጥቃት ተከትሎ ዛቻና ቁጣ በተቀላቀለበት ንግግራቸው ምን አሉ?
- የሩሲያ በሞስኮ ጥቃት ላይ የተሳተፉ አራት ሰዎች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መሰረተች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ቅዳሜ ማታ በሰጡት መግለጫቸው ላይ “የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በዩክሬን በኩል ሽብርተኞች ለማስመለጥ የሚያስችል መንገድ በድንበር በኩል ተዘጋጅቶ እንደነበረ ነው” ሲሉ ኪቭን ወቅሰዋል።
ይህንን ተከትሎ ዩክሬኑ ፕሬዝዳት ቮሊድሚር ዘለንስኪ አስተያየት በሰጡበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ንዴት ይታይባቸው የነበረ ሲሆን፤ ሀገራቸው በዚህ የሽብር ጥቃት መወቀሷ እንዳበሳጫቸው ግለጸዋል።
ዘለንስኪ በንግግራቸው፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት እና ሌሎች በሞስኮ የሚገኙ አካላት ጥቃቱን ከዩክሬን ጋር በማገናኘት “አጭበርብረዋል” ሲሉም ወቅሰዋል።
“የሩሲያ መሪ የራሱን ዜጎች ከማረጋጋት ይልቅ ጥቃቱን ኪቭ ላይ ለማላከክ መሞከሩ አሳዛኝ ነው” ሲሉም ፕሬዝዳት ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ዘለንስኪ፤ “ሩሲያውያን ዩክሬንን ከመውቀስ ይልቅ የራሳቸውን የደህንነት እና የስለላ ተቋማትን የት ነበራችሁ በማለት መጠየቅ አለባችሁ” ሱሉም ምክር ለግሰዋል።
የአርብ እለቱን የሞስኮውን ጥቃት ተከትሎ የተወሰኑ የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ መይክሃይሎ ፖዶልያክ በወቅቱ በሰጡት ምለሰሽ፤ “ዩክሬን በዚህ ተግባር ውስጥ እጇ የለበትም” ሲሉ ማስተባበላቸው ይታወሳል።
“ዩክሬን የሽብር መንገድን ተጠቅማ አታውቅም” ያሉት አማካሪው፤ “በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መፍትሄ የሚያገኙት በጦር ግንባር ነው” ብለዋል።