ዩክሬን ከምዕራባዊያን 140 ዘመናዊ ታንኮችን እንደምታገኝ ተገለጸ
አሜሪካ እና ጀርመን ብቻቸውን ከ40 በላይ ዘመናዊ ታንኮችን ለዩክሬን እንደሚሰጡ ገልጸዋል
አንዳንድ ሀገራት በሚስጥር ዘመናዊ ታንኮችን ለዩክሬን እንደሚሰጡ ተገልጿል
ዩክሬን ከምዕራባዊያን 140 ዘመናዊ ታንኮችን እንደምታገኝ ተገለጸ።
ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን ማስተናገዱ እንደቀጠለ ነው።
ሩሲያ የዩክሬንን ዋና ዋና ከተሞች እና መሰረተ ልምቶችን በሚሳኤል ማውደሟን ተከትሎ ዩክሬን ምዕራባዊያንን ድረሱልኝ ማለቷ ይታወሳል።
የዩክሬንን ጥሪ ተከትሎም ምዕራባዊያን ለሀገሪቱ አዳዲስ እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድሚትሮ ኩሌባ እንዳሉት ከወዳጅ ሀገራት እስከ 140 ዘመናዊ ታንኮችን እንደምትረከብ ተናግረዋል።
አሜሪካ 31 አብርሀም የተሰኘውን ዘመናዊ ታንክ እሰጣለሁ ስትል ጀርመን በበኩሏ 14 ሊዮፓርድ የተሰኘውን የውጊያ ታንክ እንደምትሰጥ ተገልጿል።
ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር ሜዳ ታንክ እሰጣለሁ ያሉ ሀገራትም ከወዲሁ ለዩክሬን ዉታደሮች ስልጠና መስጠት ጀምረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ብሪታንያ፣ ፖላንድ፣ ካናዳ፣ ስፔን እና ኖርዌይም ለዩክሬን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እንሰጣለን ያሉ ተጨማሪ ሀገራት ናቸው።
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የተለገሱ ማናቸውም የጦር መሳሪያዎችን አቃጥላቸዋለሁ ብላለች።
ከዚህ በተጨማሪም የምዕራባዊያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጦርነቱን ከማባባስ እና የቀጥታ ጦርነት ሊያስነሳ እንደሚችልም አስጠንቅቃለች።