ጦርነቱ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያንን ሲያፈናቅል ከ400 ቢሊዮን ዶላር በላይ ውድመት አድርሷል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ትናንት 500ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ለአንድ ሳምንት በሚል በልዩ ዘመቻ መልኩ የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መልኩን እየቀያየረ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
በጉዳቱ እና በተለያየ መንገድ በተሳተፉ ሀገራት ብዛት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውሮፓ ትልቁን ጦርነት እያካሄደች ሲሆን ጦርነቱ የዓለምን ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ አናግቷል፡፡
ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም በአውሮፓ እና አሜሪካ አስተባባሪነት ከ10 ሺህ በላይ ማዕቀቦች እና የዲፕሎማሲ መገለሎች ቢደረጉባትም ጦርነቱን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ዛሬ 500ኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን የጦርነቱ ጠባሳ ከሁለቱ ሀገራት በዘለለ የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ፣ የአውሮፓ ሀገራት የጦር መሳሪያ እጥረት እንዲገጥማቸው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱም አድርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከሁለቱም ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወታደሮች እንዲሞቱ እና እንዲቆስሉ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እስካሁን ድረስ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ እና ሌሎች ሀገራት እንዲሰደዱ ማድረጉን የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ዩክሬናዊያንን በማስጠለል ራሷ ሩሲያ ዋነኛዋ ስትሆን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የዩክሬን ዜጎችን ስታስጠልል ጀርመን አንድ ሚሊዮን፣ ፖላንድ 990 ሺህ እንዲሁም ቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ 350 ሺህ ዜጎችን አስጠልለዋል፡፡
በዚህ ጦርነት ዘጠኝ ሺህ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን ሲያጡ ከ15 ሺህ በላይ ያህሉ ደግሞ እንደቆሰሉ ተመድ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
ጦርነቱ መልኩን እየቀያየረ የቀጠለ ሲሆን ምዕራባዊያንም ዩክሬን ሩሲያን እንድታሸንፍ በየጊዜው እየሰጡት ያለውን የጦር መሳሪያ አይነት እና መጠን እያሳደጉ ይገኛሉ፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የሚሰጠው የጦር መሳሪያ እንዲቆም አስጠንቅቃ ይህ ካልሆነ ግን ወደ ኑክሌር ጦርነት ልናመራ እንችላለን ስትል አስጠንቅቃለች፡፡