“ዩክሬን ለቀጣይ 10 ዓመታት ከሩሲያ ጋር ለመዋጋት ዝግጁ ነች”- ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “ዩክሬን ድንበሯን ለሩሲያ አሳልፋ ለመስጠት ዝግጁ አይደለችም” ብለዋል
ፕሬዝዳንቱ “በርገጠኝነት ዩክሬን ጦርነቱን ታሸንፋለች” ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሊድሜር ዘለንስኪ ሀገራቸው አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለቀጣይ 10 ዓመታት ከሩሲያ ጋር ለመዋጋት ዝግጁ መሆኗን አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ ከሲ.ኤን.ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ “ዩክሬን ድንበሯን ለሩሲያ አሳልፋ ለመስጠት ዝግጁ አይደለችም” ሲሉ ተናግረዋል።
በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት መነሻው የፈረንጆቹ 2014 እንደነበረ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ መነሻውም ኪቭ የተገነጠለውን ዶንባስ ግዛት እንደገና ለመውሰድ ኦፕሬሽን በጀመረችበት ወቅት መሆኑንም አምነዋል።
“በዶንባስ የሚደረገው ጦርነት በበርካታ ምክንያቶች ለዩክሬን በጣም አስፈላጊ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ ሆኖም ግን ለግጭቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ መስጠት ተመራጭ መሆኑንም አስታውቀዋል።
“የዩክሬን ድንበርን አሳልፈን አንስጥም፤ ነገር ግን ከሩሲያ ጋር ንግግር የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ አለብን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “ንግግሮቹ ግን ሩሲያ በምታስቀምጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አይደረግም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አክለውም፤ ምንመ እንኳ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር ለቀጣይ 10 ዓመታት ለመዋጋት ዝግጁ መሆኗን ቢገልጹም ተጨማሪ ሞትን ለማስቀረት ውይይት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
በዶንባስ ክልል የሚገኘው የዩክሬን ጦር ሀገሪቱ ካላት ሰራዊት ውስጥ “ምርጡ” የሚባለው መሆኑን ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ፤ “ሩሲያ በዚህ ጦር ላይ ነው ከበባ በመፈፀም ልታጠፋው የምትፈልገው” ብለዋል።
“በጦርነቱ ዩክሬን የምታሸንፍ ይመስሎታል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ “አዎ በርገጠኝነት ዩክሬን ጦርነቱን ታሸንፋለች” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ከገቡ ዛሬ 54ኛ ቀናቸውን ይዘዋል።