ዩክሬን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሯን ጨምሮ በ108 ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከዩክሬን ህጻናትን ወደ ሩሲያ አስገድደው አስወጥተዋል ባሏቸው 37 የሩሲያ ተቋማት ላይም ማዕቀብ መጣላቸው ተገልጿል
ኬቭ ከ20 ሺህ በላይ ህጻናት ተገደው ወደ ሩሲያ እንዲገቡ መደረጉን ትገልጻለች
ዩክሬን በ37 የሩሲያ ተቋማት እና 108 ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሰዎች ውስጥ የዩክሬን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማይኮላ አዛሮቭ ይገኙበታል።
ውሳኔው ከዩክሬን ህጻናትን አስገድደው ወደ ሩሲያ ያስገቡ ሰዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ማዕቀብ የተጣለባቸውን ሰዎች በዝርዝር ባይናገሩም ፊርማቸው ያረፈበት ሰነድ በግለሰቦቹ ላይ ከአምስት እስከ 10 አመት እስራት ቅጣት መተላለፉ ተመላክቷል።
ከእስር ቅጣቱ ባሻገር የሃብት እገዳን ጨምሮ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችም ተጥለዋል።
አብዛኞቹ አዲስ ቅጣት የተላለፈባቸው የሩሲያ ዜግነት ያላቸው ሰዎችም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ቅጣት የተላለፈባቸው መሆናቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የቀድሞው የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ማይኮላ አዛሮቭ እና በየካቲት ወር የዩክሬን ዜግነታቸውን የተነጠቁት የቀድሞው የትምህርት ሚኒስትር ዲሚይትሮ ታባቺንክ ቅጣት ከተላለፈባቸው 108 ሰዎች መካከል ናቸው ተብሏል።
የክሬሚያ እና ሉሃንስ ግዛት አስተዳዳሪዎችም የተለያዩ ማዕቀቦች ተጥሎባቸዋል የተባለ ሲሆን፥ 37ቱ የሩሲያ ተቋማት ደግሞ በህጻናት ላይ የሚሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።
ኬቭ 20 ሺህ የሚጠጉ ዩክሬናውያን ህጻናት ያለወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ፈቃድ ወደ ሩሲያ እና ሩሲያ ወደተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ተገደው እንዲገቡ መደረጉን ታምናለች።
የአሜሪካው የል ዩኒቨርሲቲ ከቀናት በፊት ባወጣው ጥናትም ከ2 ሺህ 400 በላይ ዩክሬናውያን ህጻናት ወደ ቤላሩስ በሃይል መወሰዳቸውን ይፋ አድርጓል።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዩክሬናውያን ህጻናት ወደ ሩሲያ ተገደው ገብተዋል በሚል በመጋቢት ወር በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።