ሩሲያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ለ45 ሀገራት ጦር መሳሪያ ሸጣለች
የጦር መሳሪያ በመሸጥ ከዓለም ሁለተኛ የሆነችው ሩሲያ ከ2016 እስከ 2020 ለ45 ሀገራት ጦር መሳሪያ መሸጧ ተገልጿል።
ሩሲያ በአምስት ዓመታት ውስጥ 28 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያን መሸጧ የተገለጸ ሲሆን በጥቅሉ የዓለምን 20 በመቶ የመሳሪያ ሽያጭ አካናውናለች።
በርካታ የዓለም ሀገራት ከሩሲያ የቶር መሳሪያ ግዢ የሚፈጽሙ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ሕንድ ከፍተኛውን ግዥ በማከናወን ቀዳሚውስ ስፍራ እንደምትይዝ የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ከሕንድ በመቀጠል ቻይና ፣አልጀሪያ፣ ግብፅ እና ቬትናምም በከፍተኛ ደረጃ የሩሲያን የጦር መሳሪያዎች የሚገዙ ሀገራት እንደሆኑም ተገልጿል።
ሩሲያ ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ የዓለም የጦር መሳሪያ ሻጭ ሀገር መሆኗም በሪፖርቱ ተገልጿል። ሞስኮ ለ10 ሀገራት 90 በመቶ የመሳሪያ ሽያጭ እንደምታከናውንም ተመላክቷል።
ሕንድ ከዚህ ውስጥ 23 በመቶ የሚሆነውን እየገዛች ነው ተብሏል። ሕንድ ካላት አጠቃላይ የጦር መሳሪያዎች 49 ነጥብ 3 የሚሆነው ከሩሲያ የሚገባ እንደሆነው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ሕንድ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ወጭ በማድረግ ከሩሲያ የጦር መሳሪያ የገዛች ሲሆን፤ ጎረቤቷ ቻይናም 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ወጭ በማድረግ ከሞስኮ መሳሪያ ገዝታለች።
ሁለቱ የአፍሪካ ሀገራት ግብፅ እና አልጀሪያ በቅደም ተከተል ባለፉት ዓመታት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን እና 3 ነጥብ 3 ዶላር የጦር መሳሪያን ከሩሲያ ገዝተዋል። ቬትናም ባለፉት አምስት ዓመታት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ከሞስኮ አስገብታለች።
ሩሲያ ከምትሸጠው የጦር መሳሪያ 48 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው የጦር አውሮፕላን እንደሆነም ተገልጿል።
ከ2016 እስከ 2020 ሩሲያ ሚግ ሱክሆይ እና ሚግን ጨምሮ 400 ተዋጊ ጀቶችን ለ13 ሀገራት መሸጧ ይፋ ተደርጓል። ከነዚህ መካከል ግማሽ ሚሆኑትን ጀቶች ሕንድ ገዝታቸዋለች ተብሏል።
ከሩሲያ የጦር መሳሪያ ከሚገዙ ሀገራት መካከል ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ አልጀሪያ፣ ግብፅ እና አንጎላ የተካተቱ ሲሆን ቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ኢራን፣ ሶሪያም ከሞስኮ መሳሪያ ያስገባሉ።
ሩሲያ ከምትሸጣቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል የጦር አውሮፕላኖች፣ ሚሳኤሎች፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና የአየር ወቃወሚያ ይገኙባቸዋል።
ከሩሲያ የጦር መሳሪያዎች መካከል አንዱና ታዋቂው ኤኬ 47 ወይም ክላሽንኮቭ ሲሆን በኢትዮጵያ በብዙ ቦታዎች ጥቀም ላይ እየዋለ ነው።