ዩክሬን የተሰረቀ እህል የጫነች መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች
የካሜሮን ሰንደቅ አላማን የምታውለበልበው መርከብ ሩሲያ የዩክሬን እህልን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የምታመላልስባት ነበረች ተብሏል
የመርከቧ ካፒቴን እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት እንደሚጠብቀው ተገልጿል
ዩክሬን የተሰረቀ እህል የጫነች መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታወቀች።
የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት (ኤስቢዩ) ሩሲያ ከተቆጣጠረቻት ክሬሚያ የተነሳችው መርከብ በዩክሬን ኦዴሳ ግዛት ስታልፍ በቁጥጥር ስር መዋሏን ይፋ አድርጓል።
የካሜሮን ሰንደቅ አለማ የምታውለበልበው “Usko Mfu” የጭነት መርከብ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት እንዳላት አገልግሎቱ ገልጿል።
ከ2023 ጀምሮም ከሴባስታፖል “ሩሲያ ከዩክሬን የዘረፈችውን እህል ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ስታመላልስ ነብር” ብሏል ተቋሙ ያወጣው መግለጫ።
መርከቧ ጉዞ ስትጀምር የአቅጣጫ አመላካች መሳሪያዋን (ጂፒኤስ ትራከር) በተደጋጋሚ እንደምታጠፋና ሀሰተኛ የጉዞ መረጃ እንደምታስተላልፍም ጠቅሷል።
ዩክሬን “በውሃ ግዛቴ ገብታለች” ያለቻት የጭነት መርከብ ጉዞ እንዴት እንደተገታ በዝርዝር አልገለጸችም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሩሲያ በ2022 በዩክሬን ጦርነት ካወጀች በኋላ ከተቆጣጠረችው የደቡባዊ ዩክሬን አካባቢዎች በስፋት የሚገኝ የእህል ምርትን ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ ኬቭ በተደጋጋሚ ትከሳለች።
የተቆጣጠረቻቸውን ግዛቶች የግዛቷ አካል ያደረገችው ሞስኮ ግን በኬቭ በኩል “ዝርፊያ” ነው ተብሎ የሚቀርበውን ውንጀላ አትቀበለውም።
በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር ውላለች የተባለችው መርከብ ዋና መሪ (ካፒቴን) እና 12 ሰራተኞች ይዛ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፥ አዘርባጃናዊው የመርከቧ ካፒቴን እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል ተብሏል።
የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት (ኤስቢዩ) በህገወጥ ድርጊቱ የሚሳተፉ ሌሎች አካላትን ለመለየት ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
ለበርካታ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ሀገራት ስንዴ በስፋት የምትልከው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ምርቷን ለአለማቀፍ ገበያ ለማቅረብ ተቸግራለች።
በመንግስታቱ ድርጅት እና ቱርክ አደራዳሪነት በጥቁር ባህር የግብርና ምርቷን ለውጭ ገበያ እንድታቀርብ ከሩሲያ ጋር የተደረሰው ስምምነትም ባለፈው አመት መጠናቀቁ ይታወሳል።