ለሳምንታት በአዞቭስታል የብረት ፋብሪካ ውስጥ መሽገው የነበሩ የዩክሬን ወታደሮች እጅ ሰጡ
ወታደሮቹ ላለፉት ሳምንታት በሩሲያ ጦር ተከበው እጅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ነበር
300 የዩክሬን ወታደሮች በአካባቢው ላለው የሩሲያ ጦር እጅ ሰጥተዋል ተብሏል
በዩክሬኗ ማሪዩፖል ከተማ በአዞቭስቶል የብረት ፋብሪካ ውስጥ መሽገው የነበሩ የዩክሬን ወታደሮች ለሩሲያ ወታደሮች እጅ ሰጥተዋል፡፡
ዩክሬን የሰሜን ቃል ኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከ82 ቀናት በፊት ከሩሲያ ጋር ወደ ለየለት ጦርነት የገቡት፡፡
የዩክሬኗ ማሪዮፖል ከተማ የሩሲያ የአየር ላይ ጥቃቶችን በመፍራት መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን የዩክሬን ጦር አባል የሆኑ እና ከተለያዩ ሀገራት ለዩክሬን ድጋፍ ለመስጠት በሚል ወደ ኬቭ የመጡ ወታደሮች ግን በዚች ከተማ ከሩሲያ ጦር ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል፡፡
ማሪዮፖል ከተማን የተቆጣጠረው የሩሲያ ጦርም በዚች ከተማ ባለ አንድ የብረት ፋብሪካ የመሸገው የዩክሬን ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡
ተጨማሪ ሀይል ከሩሲያ ከበባ ነጻ እንዲያወጧቸው ተስፋ አድርገው ሲጠብቁ የነበሩ 250 የዩክሬን ወታደሮች ለሩሲያ ጦር አጅ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው 265 የዩክሬን ወታደሮች ለሩሲያ ጦር አጅ መስጠታቸውን ገልጸው ተጨማሪ የቆሰሉ 51 ወታደሮችም አጅ ስጥተዋል ብለዋል፡፡
እነዚህ እጅ የሰጡ የዩክሬን ምርኮኛ ወታደሮች በዶንቴስክ እና ሉሃን ግዛቶች ባሉ ሆስፒታሎች ህክምና እያገኙ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው የአዞቭቶል ብረት ፋብሪካን የመከላከል ስራው ማብቃቱን ገልጸው ይህን ያደረጉት ጀግና ዩክሬናዊያን በህይወት እንዲቆዩ በማሰብ ነውም ብለዋል፡፡
የተማረኩት የዩክሬን ወታደሮች ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በሚያዙት መሰረት እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የዩክሬን ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከሩሲያ ጋር በመነጋገር የእስረኞች ልውውጥ እንደሚደረግ እና በሩሲያ እጅ ስራ የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች ወደቤታቸው ይመለሳሉ ብለዋል፡፡