ሩሲያ ከባልቲክ ባህር ሀገራት ም/ቤት መውጣቷን ገለጸች
ስብስቡ ከተመሰረተ 30 ዓመት ሆኖታል
የባልቲክ ሀገራት ም/ቤት 11 አባላት አሉት
ሩሲያ፤ የአውሮፓ ኮሚሽንን ጨምሮ 11አባላት ያሉበትን የባልቲክ ባህር ሀገራት ምክር ቤት ለቃ መውጣቷን የሩሲያ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከሰሞኑ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ን እንደሚቀላቀሉ የገለጹት ስዊድንና ፊንላንድን ጨምሮ 11 አባላት ያሉት ስብስብ ነው፡፡
ሩሲያ ከስብስቡ ለመውጣት ገፊ ምክንያት እንደሆነ የገለጸችው በምክር ቤቱ ያለው ሁኔታ እተባባሰ መምጣቱን ነው ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገራት በምክር ቤቱ እኩል ውይይት እንዳይደረግ እንቅፋት መሆናቸውንም ሩሲያ ገልጻለች፡፡ በዚሁ መሰረት ሩሲያ ከዚህ ምክር ቤት መውጣቷን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የባልቲክ ባህር ሀገራት ም/ቤት ቀጠናው ጸጥታው የተጠበቀ፤ ዘላቂና የበለጸገ እንዲሆን ለማድረግ የተቋቋመ ምክር ቤት ነው፡፡በዚህ ምክር ቤት ውስጥ አባል የሆኑት ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ አይስላንድ፣ ላቲቪያ፣ ሊታኒያ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ሩሲያ፣ ስዊድን እና የአውሮፓ ኮሚሽን ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ የተቋቋመው በፈረንጆቹ መጋቢት 16 ቀን 1992 በዴንማርክ መዲና ኮፐንሃገን ሲሆን፤ አሁን ላይ ዋና መስሪያ ቤቱ በስዊዲን ዋ ከተማ ስቶክሆልም ነው፡፡