ሩሲያውያን ከመጪው ወር መባቻ ጀምሮ ያለ ቪዛ ወደ ዩክሬን አይገቡም ተብሏል
ዩክሬን ከመጪው ሃምሌ ጀምሮ ሩሲያውያን ያለ ቪዛ ወደ ሃገሯ እንደማይገቡ አስታወቀች፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከመጪው ሃምሌ 1 ጀምሮ ሩሲያውያን በቪዛ ብቻ ወደ ዩክሬን እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡
መንግስታቸው ጉዳዩን የተመለከተ ውሳኔ ዛሬ አርብ እንደሚሳልፍም ዜሌንስኪ በይፋዊ የቴሌግራም ገጻቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
እርምጃው ዩክሬን ከሶቪዬት ህብረት ተለይታ ነጻነቷን ካወጀችበት ከፈረንጆቹ 1991 ጀምሮ ያለ ቪዛ ሲወጡ ሲገቡ የነበሩ ሩሲያውያንን የሚያግድ ነው ተብሏል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችውን ዘመቻ ከጀመረች አራት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ እርምጃው ይሄንኑ ተከትሎ የሚወሰድ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡
ሩሲያ ወደ ሙሉ ማጥቃት መሸጋገሯን ተከትሎ የሃገሪቱን ደህንነት ለመቆጣጠር የሚወሰድ እርምጃ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡
"ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሀገራችን ብሄራዊ ደህንነት፣ ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል በማሰብ ካቢኔያችን የሩሲያ ዜጎች ወደ ዩክሬን የሚገቡበትን ስርዓት እንዲከልስ ሀሳብ አቅርቤ ነበር" ሲሉ ጽፈዋል ዜሌንስኪ፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን 2 ሺ 300 ኪሎ ሜትር ገደማ ድንበርን ይጋራሉ፡፡ ከዚህም በላይ በደም የተሳሰሩ ቤተሰባዊ ዝምድና ያላቸው ናቸው፡፡
ሆኖም ሩሲያ በ2014 ክሬሚያን ወደ ራሷ ግዛት ከቀላቀለች በኋላ ወደ ዩክሬን የሚገቡ ሩሲያውያን ቁጥር በእጅጉ ማሽቆልቆሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡