ሩሲያ ምዕራባውያን ንብረቷን የሚወርሱ ከሆነ "ከባድ" ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠነቀቀች
የአውሮፖ ህብረት እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገው የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ንብረት የተገኘውን ወለድ ለዩክሬን ለመላክ የሚያስችል ህግ አጽድቋል
አሜሪካ እና አውሮፖውያን በ10 ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠረውን የሩሲያን ንብረት የሚወርሱ ከሆነ ሞስኮ ጠንካራ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች
ሩሲያ ምዕራባውያን ንብረቷን የሚወርሱ ከሆነ "ከባድ" ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠነቀቀች።
አሜሪካ እና አውሮፖውያን በ10 ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠረውን የሩሲያን ንብረት የሚወርሱ ከሆነ ሞስኮ ጠንካራ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች።
የአውሮፖ ህብረት በትናንተናው እለት እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገው የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ንብረት የተገኘውን ወለድ ለዩክሬን ለመላክ የሚያስችል ህግ ማጽደቁን ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ እና አጋሮቿ በምዕራቡ አለም የሚገኘውን 300 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለውን የሩሲያ ሀብት እንዳይንቀሳቀስ እግድ መጣላቸው ይታወሳል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ የምዕራባውያንን ድርጊት "ስርቆት" ነው ሲሉ ተናግረዋል።
"ይህ የራስህ ያልሆነ ነገርን የመውሰድ ተግባር ነው" ብለዋል።
ማሪያ ዛካሮቫ ምዕራባውያን ንብረት ወደመውረስ የሚሸጋገሩ ከሆነ ሩሲያ እድግ "ከባድ የሆነ ምላሽ" እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
"ሀገራችን ይህንን እንደስርቆት ስለምታየው፣ የምትሰጠው ምላሽም በሌቦች ላይ እንደሆነ አድርጋ እንደምትቆጥረው" ዛካሮቫ ተናግረዋል።
ሩሲያ ከዚህ ቀደም ምዕራባውያን ንብረቷን የሚወርሱባት ከሆነ የአሜሪካን፣ የምዕራባውያን እና የሌሎችን ንብረት በምላሹ እንደምትወርስ መግለጿ ይታወሳል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ለዩክሬን አጋርነት ለማሳየት በርካታ ማዕቀቦችን በሩሲያ ላይ ጥለዋል።
ሩሲያም ግን ማዕቀቦቹ የጋራ ጉዳት ማስከተላቸውን ስትገልጽ ቆይታለች።