በዩክሬን ቤተ-መጻህፍት ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት 44 በመቶ ያህሉ በሩሲያኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው
ዩክሬን ከሶቭየት ዘመን የመጡ ወይም በሩሲያኛ የተጻፉ 19 ሚሊዮን የሚሆኑ መጽሀፎችን እስከ ባለፈው ህዳር ወር ድረስ ከቤተ-መጻህፍት ማስወገዷ ተነግሯል።
የሀገሪቱ ፓርላማ የሰብዓዊ እና የመረጃ ፖሊሲ ኮሚቴ ምክትል ኃላፊ ኢቭሄኒያ ክራቭቹክ፥ ከ19 ሚሊዮን መጽሐፍቶች ውስጥ 11 ሚሊዮን የሚሆኑት በሩሲያኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው ብለዋል።
ክራቭቹክ በሀገሪቱ ፓርላማ ድረ-ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ ከሶቪየት የግዛት ዘመን አንዳንድ የዩክሬንኛ ቋንቋ መጻህፍትም እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።
"በተጨማሪም በዩክሬን ላይ የትጥቅ ጥቃቶችን የሚደግፉ ደራሲዎች መጽሀፎቻቸውን ለማስወገድና ዳግም ለመጻፍ ምክሮች አሉ" በማለት ገልጸዋል።
የተወገዱት መጽሀፍት ላይ ምን እንደተደረገ እስካሁን አልታወቀም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በፈረንጆች 2014 ሩሲያ ክሬሚያን ከግዛቷ ጋር ለመቀላቀል ከተንቀሳቀሰች በኋላ ኬቭ የሩስያ መጻህፍትን መጠቀምን የበለጠ ገድባለች ተብሏል።
እ.ኤ.አ. በ2022 አጋማሽ ላይ ዩክሬን ማንነቴን ያዳፈኑ ናቸው ያለቻቸውን የሩሲያ መጽሀፍት ስርጭት መገደቧም በዘገባው ተወስቷል።
ይህ እርምጃዋም በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለውን የባህል ትስስር እንዲላላ ያደርገዋል በሚል ተሰግቷል።
በዩክሬን ቤተ-መጻህፍት ውስጥ 44 በመቶ ያህሉ መጻሕፍት በሩሲያኛ የተጻፉ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ደግሞ በዩክሬን ወይም በአውሮፓ ህብረት ሀገራት ቋንቋዎች የተጻፉ መሆናቸው ተነግሯል።