ፖለቲካ
ፕሬዝዳንት ባይደን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም 20 በመቶውን የዩክሬን ግዛት ለፑቲን ማቅረባቸው ተነገረ
ኪየቭ እና ሞስኮ ቀረበ የተባለውን ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል ተብሏል
ኪየቭ ግዛቷን ለመከፋፈል ፍቃደኛ እንዳልነበረች ተነግሯል
የአሜሪካ የስለላ ተቋም (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ዊልያም በርንስ ለሩሲያው ፕሬዝዳን ፑቲን አንድ አምስተኛውን የዩክሬን ግዛት ለጦርነቱ መፍትሄ አድርገው ማቅረባቸው ተዘግቧል።
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስም ተዘጋጀ በተባለው የሰላም እቅድ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ለፕሬዝዳንት ፑቲን የዩክሬንን 20 በመቶ መሬት ለመስጠት ተሞክሯል ነው የተባለው
ዳይሬክተር በርንስ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር የተጀመረውን ጦርነት ለማቆም እቅዱን አስቀድመው በጥር አጋማሽ ላይ እንዳቀረቡ ይታመናል ሲል ምንጮቹን ጠቅሶ ኒውስ ዊክ ዘግቧል።
ጉዳዩን ኤንዜድዜድ የተባለ የስዊዘርላንድ-ጀርመን ጋዜጣ የጀርመንን ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ፖለቲከኞችን በመጥቀስ ዘግቧል።
ኪየቭ እና ሞስኮ ቀረበ የተባለውን ይህን ሀሳብ ውድቅ አድርገውታል ተብሏል።
እንደ ጋዜጣው ከሆነ እቅዱ በግምት የዩክሬን ምስራቃዊ ዶንባስ ክልልን ይሆናል የተባለ 20 በመቶው የኪየቭን ግዛት ለሞስኮ አቅርቧል።
ኪየቭ ሀሳቡን ውድቅ አድርጋለች የተባለም ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያቱ "ግዛታቸውን ለመከፋፈል ፍቃደኞች ስላልነበሩ ነው" ተብሏል።
የሩሲያ ባለስልጣናት ደግሞ በምንም መልኩ ጦርነቱን በረጅም ጊዜም ቢሆን እናሸንፋለን የሚል እምነት እንደነበራቸው ተዘግቧል።