ሩሲያ የዩክሬንን ጦር ከድንበሯ ብዙ ማራቅ እንደምትፈልግ ገለጸች
የዩክሬን ፕሬዝዳንት የምዕራባዊያን ጫና ስላለባቸው ውሳኔዎችን በራሳቸው መወሰን እንደማይችሉም ተገልጿል
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል
ሩሲያ የዩክሬንን ጦር ከድንበሯ ብዙ ማራቅ እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከስፑትኒክ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ የሩሲያ ቻይና ወዳጅነት እና ሩሲያ ከምዕራባዊያን ጋር ስላላት ውጥረት በቃለ መጠይቃቸው ትኩረት ያደረጉባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡
ላቭሮቭ በዚህ ጊዜ፥ ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት በውይይት የመቋጨት ፍላጎት የነበራት ቢሆንም በምዕራባዊያን ተጽዕኖ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ባሳለፍነው ሚያዝያ ላይ ሩሲያ እና ዩክሬን ልዩነቶቻቸውን በውይይት ለመፍታት ቢሞክሩም በውጭ ተጽዕኖ ምክንያት እንደተቋረጠ ያነሱት ላቭሮቭ፥ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ የመወሰን ነጻነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ምዕራባዊያን የዩክሬን ጦርነት እንዲቀጥል በመፈለጋቸው ምክንያት ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሞስኮ ይህን ጦርነት በድል መቋጨት የሚያስችላት የጦር መሳሪያ ክምችት አላትም ብለዋል፡፡
የሩሲያዊያንን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ሲባልም በድንበር አቅራቢያ ያለውን የዩክሬን ጦር ድንበር አካባቢ እንደምታርቅም ላቭሮቭ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
የሩሲያ-ቻይና ወዳጅነት ገደብ አልባ በሆነ መንገድ መቀጠሉን ያነሱት ሰርጊ ላቭሮቭ፥ ሁለቱ ሀገራት በነዳጅ ንግድ፣ በጠፈር ምርምር፣ በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘርፎች ትብብራቸውን ቀጥለዋልም ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደርሊን በአውሮፓ ለደረሰው የኢኮኖሚ ድቀት በሩሲያ ሽንፈት ይካካሳል ማለታቸውን ሰርጊ ላቭሮቭ በቃለ መጠይቃቸው ላይ ተችተዋል፡፡