ዩክሬን ከአሜሪካ የተለገሳት አብርሀም ታንክን ከጦር ግንባር አስወጣች
ሀገሪቱ ታንኩን ከጦር ግንባር ያስወጣችው በሩሲያ ድሮን እንዳይመታባት በማሰብ ነው
የምድር ላይ ጦርነቶችን ይቀይራሉ የተባሉት ሊዮፓርድ እና አብርሀም ታንኮች በሩሲያ ርካሽ ድሮኖች እየወደሙ ነው ተብሏል
ዩክሬን ከአሜሪካ የተለገሳት አብርሀም ታንክን ከጦር ግንባር አስወጣች።
ሩሲያ እና ዩክሬን የአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የጀመሩት ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል።
ይህ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ እንደቀጠለ ሲሆን የተሳታፊ ሀገራት ድጋፍም ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቷል።
ጦርነቱን ሩሲያ ካሸነፈች ለአውሮፓ የደህንነት ስጋት ይደቅናል በሚል የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ አባል ሀገራት በተለያየ መንገድ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በተለይም ዩክሬን የምድር ላይ ውጊያዎች በሩሲያ የበላይነት እየተወሰደባት ነው በሚል እና ይህን ለመቀልበስ ምዕራባዊያን ሀገራት የጦር ታንኮችን ሲለግሱ ቆይተዋል።
ከተለገሱ ውድ የጦር ታንኮች መካከል ጀርመን ሰራሹ ሊዮፓርድ እና አሜሪካ ሰራሹ አብርሀም ታንኮች ዋነኞቹ ናቸው።
እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳላቸው የተነገረላቸው እነዚህ ታንኮች 500 ዶላር ዋጋ አላቸው በተባሉ የሩሲያ ድሮኖች እየተመቱ እንደሆነ ተገልጿል።
ዩክሬንም እነዚህ ውድ የጦር ታንኮች ከሩሲያ ድሮኖች ለመጠበቅ ከጦር ግንባሮች ወደ ኋላ እያሸሸች እንደሆነ ቪኦኤ ዘግቧል።
አሜሪካ ለዩክሬን ከሰጠቻቸው 31 አብርሀም ታንኮች መካከል አምስቱ በሩሲያ ድሮን ተመተዋል የተባለ ሲሆን ቀሪዎቹን ታንኮች ለማዳን ጥረት እየተደረገ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን ጥቃት እንድትቋቋም ሌላ መፍትሔ እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ያለውን ጦርነት በበላይነት እንድታጠናቅቅ በአሜሪካ አስተባባሪነት ድጋፍ የሚያደርጉ 50 ሀገራት እንዳሉም ተገልጿል።
አሜሪካ ከሰሞኑ ለዩክሬን 6 ቢሊዮን ዶላር የረጅም ጊዜ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጿ ይታወሳል።
ከዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላሩ ለድሮን ጥቃት መከላከያ እና የመልሶ ማጥቃት እቅዶችን ለመንደፍ እንደሚውል ተገልጿል።
እንዲሁም አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ድጋፍ ማድረጓን አስታውቃለች።