የዩክሬን ወታደሮች "እንዴት ማስደንገጥ እንዳለባቸው ያውቃሉ"-ዘለንስኪ
የሩሲያ ጦር ከ100 በላይ ወታደሮች መግደሉን እና ሌሎች 200 የሚሆኑ ማቁሰሉን አስታውቋል
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የዩክሬን ጦር "በድንገት" ውጤት የማምጣት አቅሙን በትናትናው እለት አድንቀዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የዩክሬን ወታደሮች "እንዴት ማስደንገጥ እንዳለባቸው ያውቃሉ" አሉ።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ የዩክሬን ጦር "በድንገት" ውጤት የማምጣት አቅሙን በትናትናው እለት አድንቀዋል።
ፕሬዝደንቱ ኪቭ ድንበር አቋራጭ የሆነ ጥቃት ፈጽማለች ስለሚለው በሩሲያ ስለቀረበው ክስ አላነሱም።
ሩሲያ፣ የዩክሬን ጦር ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ድንበር አቋርጦ ኩርስክ የተባለችውን ግዛቷን ወርሮ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ብትገልጽም፣ ዩክሬን ዝምታን መርጣለች።
"የዩክሬን ጦር እንዴት ማሰደንገጥ እንደሚችል ሁሉም ያውቃል። እንዴት ውጤት ማምጣት እንዳለበትም ያውቃል" ብለዋል ዘለንስኪ።
ዘለንስኪ "ወታደሮቻችን ከፍተኛ ኃይል ያለውን የወራሪ ኃይል መመከት ብቻ ሳይሆን ዩክሬንን ለመጠበቅ አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚችል በጦር ሜዳ ታይቷል" ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ጦር ወደ ደቡብ ምዕራብ ሩሲያ ዘልቆ መግባቱን እና ይህም "ከባድ ጸብ አጫሪ ድርጊት" እንደሆነ ተናግረዋል።
ዩክሬን አድርሳዋለች የተባለው ጥቃት ኩርስክ በተባለችው የሩሲያ ግዛት የአስቸኳይ አዋጅ እንዲታወጅ አስገድዷል። የዩክሬን ወታደሮች ወደ ግዛቷ የገቡት ከአንድ ሺህ በላይ እግረኛ ሰራዊት እና በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ይዘው እንደነበር ተገልጿል።
የሩሲያ ጦር ከ100 በላይ ወታደሮች መግደሉን እና ሌሎች 200 የሚሆኑ ማቁሰሉን አስታውቋል። ከሁለት አመት በላይ ባስቆጠረው የዩክሬን- ሩሲያ ጦርነት፣ የዩክሬን ጦር ወደ ሩሲያ ግዛት በመግባት ከባድ የተባለ ጥቃት ሲያደርስ ይህ የመጀመሪያው ነው።