ዩክሬን ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ በመግባት የአየር ጦር ሰፈር መደብደቧን ገለጸች
ኪቭ በሩሲያ የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ ጥቃት እያደረሰች ያለችው፣ ሩሲያ የጦር አውሮፕላኖቿን ተጠቅማ የምታደርሰውን የማጥቃት አቅም ለማዳከም ነው
የሩሲያ ሱ-34፣ ሱ-35 እና ሚግ-31 አውሮፕላኖች በዚህ የአየር ጦር ሰፈር እንደነበሩ የዩክሬን ጦር ገልጿል
ዩክሬን ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ በመግባት የአየር ጦር ሰፈር መደብደቧን ገለጸች።
የዩክሬን ጦር በምዕራብ ሩሲያ በሊፕስክ ግዛት በሚገኘው የአየር ጦር ሰፈር ላይ ሌሊቱን ባደረሰው ድብደባ ቦምቦችን ማውደሙን እና በርካታ ፍንዳታዎችን ማድረሱን ገልጿል።
ኪቭ በሩሲያ የአየር ኃይል ሰፈሮች ላይ ጥቃት እያደረሰች ያለችው፣ ሩሲያ የጦር አውሮፕላኖቿን ተጠቅማ የምታደርሰውን የማጥቃት አቅም ለማዳከም ነው።
"ከፍተኛ እሳት ሲነሳ እና ፍንዳታ ሲከሰት ታይቷል" ብሏል የኪቭ ጦር በቴሌግራም ገጹ። የሩሲያ ሱ-34፣ ሱ-35 እና ሚግ-31 አውሮፕላኖች በዚህ የአየር ጦር ሰፈር እንደነበሩ ጦር ገልጿል።
በደርዘን የሚቆጠሩ አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች እንዲሁም 700 ጋይድድ ቦምቦች በሚገኙበት በዚህ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት የደረሰው በድሮን መሆኑን ሮይተርስ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሩሲያዋ ሊፕስክ ግዛት አስተዳዳሪም የጥቃቱን መፈጸም አረጋግጠዋል።
አስተዳዳሪው ኢጎር አርታሞኖብ በዩክሬን ድሮኖች በደረሰው ከባድ ጥቃት ፍንዳታ መከሰቱን፣ የኃይል አቅርቦት መቋረጡን እና ዘጠኝ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል። የሩሲያው ኢንተርፋክስ ዜና አገልግሎት የአካባቢውን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጠቅሶ እንደዘገበው በግዛቷ ዋና ከተማ ዳርቻ የእሳት አደጋ ተቀስቅሶ ነበር።
ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ የኪቪ ጦር ድንበር በማቋረጥ ኩርስክ በተባለችው የሩሲያ ግዛት ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ ነው ስትል ሞስኮ ከሳለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ጥቃት ማድረሷን በቀጥታ ባይናገሩም፣ የዩክሬን ጦር "እንዴት ማስደንገጥ እንዳለበት ያውቃል" ሲሉ ለጦሩ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ድርጊቱን "አደገኛ ጸብ አጫሪነት" ሲሉ የገለጹት ፕሬዝደንት ፑቲን የገባው የዩክሬን ጦር ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።