ዩክሬን በዚህ ሳምንት በሙስኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ትጀምራለች - ዜለንስኪ
ዩክሬን በአለም አቀፉ የሙስና ደረጃ ከ180 ሀገራት 122ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
ፕሬዝዳንቱ በጦርነቱ ምክንያት በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናት ተበራክተዋል መባሉን ተከትሎ ነው እርምጃው ይወሰዳል ያሉት
ሙስና ስር የሰደደ ችግር የሆነባት ዩክሬን በዚህ ሳምንት ጥብቅ እርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ “ሙስኞችን አንታገስም፤ እንደከዚህ ቀደሙ በመንግስት ተቋማት የሚሰሩና የህዝብን ሀብት የሚዘርፉ አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ አረጋግጥላችኋለሁ” ብለዋል።
ከወታደሮች ምልመላ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሙስና ተዘፍቀዋል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው ዜለንስኪ መግለጫ የሰጡት።
ዩክሬን ከፍተኛ ሙስና የሚታይባት እና የመንግስት መዋቅሯም በዚሁ ችግር የሚፈተንባት ሀገር ናት።
የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያሳየው፥ ኬቭ በ2021 ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑ 180 ሀገራት 122ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የአውሮፓ ህብረት ባለፈው አመት ዩክሬንን በእጩ አባልነት ሲመዘግባት ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የጸረ ሙስና የሪፎርም ስራዎች በትኩረት ልትሰራ ይገባል የሚለው አንዱ ነው።
ነገ 11ኛ ወሩን የሚይዘው ከሩሲያ ጋር የገባችበት ጦርነት የሀገሪቱን የሙስና ፈተና ማወሳሰቡን ሬውተርስ ዘግቧል።
በ2019 በምርጫ ስልጣን የያዙት ዜለንስኪ በምርጫ ቅስቀሳቸው ቃል የገቡትን የጸረ ሙስና ትግል በስፋት አልሄዱበትም በሚል ይተቻሉ።
ወደ ስልጣን እንደመጡ የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የቀረበባቸውን የሙስና ወንጀል አምነው ስልጣን ከመልቀቃቸው ውጭ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ በሌብነት የተዘፈቁ ዩክሬናውያን ተጠያቂ ሲሆኑ አልታየም።
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ በትናንቱ መግለጫቸው ግን “ይህ ሳምንት ወሳኝ የሚባሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ነው” ብለዋል።
“ውሳኔዎቹ ተዘጋጅተው ተጠናቀዋል፤ ነገር ግን አሁን ለህዝብ ይፋ ማድረግ አልፈልግም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ የሀገሪቱ የክልላዊ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ቫስሊ ሎዚንስኪ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው እየተነገረ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ኦሌክሲ ሬዥኒኮቭም በሙስና መጠርጠራቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ ይገኛሉ።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ግን ውንጀላውን ያስተባበለ ሲሆን፥ የሀገሪቱ ፓርላማ ምርመራ እንዲደረግ አዟል ነው የተባለው።