በሳህል ቀጠና 18 ሚሊዮን ሰዎች ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተመድ አስጠነቀቀ
7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት በምግብ እጦት ሊሰቃዩ እንደሚችሉም ተመድ አሳስቧል
አደጋው እንደፈረንጆቹ ከ2014 ወዲህ ከፍተኛው ቀውስ ሊሆን እንደሚችልም ነው የተገለጸው
በሳህል ቀጠና 18 ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠነቀቀ፡፡
የድርጅቱ የምግብ ፕሮግራም (wfp) በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ባለው ከፊል ደረቃማ አካባቢ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መሰረታዊ ምግቦች በበቂ ሁኔታ እንዳይዳረሱ በቀጠናው የሚከሰቱ ግጭቶች ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ዋጋ ንረት ዋናኛ ማነቆዎች ሆነው መቆየታቸው አስገንዝቧል፡፡
ዓለም አቀፍ ለጋሾች ተጨማሪ ገንዘብ መልቀቅ ካልቻሉ አደጋው የከፋ እንደሚሆንም ፕሮግራሙ አሳስቧል፡፡
በአንዳንድ የተጎዱ አከባቢዎች የምግብ አቅርቦት መቋረጡን የገለጸው ደብሊው.ኤፍ.ፒ ፤አሁን ባለው ሁኔታ በድጎማ መልክ ራሽን ያገኙ በነበሩ አከባቢዎች ሳይቀር እርዳታ ማግኘት የማይችሉበት ከባድ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲ (ኦቻ) ቃል አቀባይ ጄንስ ላርኬ "በአፍሪካ ሳህል ቀጠና እስከ 18 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ይገጥማቸዋል" ብለዋል፡፡ ቁጥሩ እንደፈረንጆቹ ከ2014 ወዲህ ከፍተኛ ነው ተብሎለታል፡፡
እንደ ላርኬ ገለጻ በሳህል ውስጥ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ከ5 አመት በታች ያሉ ህጻናት ለምግብ እጦት ሊዳረጉ ይላሉ በሚል ተሰግቷል፡፡
አሁን ላይ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ተዳርገዋል; ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉና የእርዳታ ስራዎች ካልተጠናከሩ ደግሞ በዚህ አመት መጨረሻ ይህ ቁጥር ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ተብሏል፡፡
በቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ማሊ እና ኒጀር ችግሩ የአደጋ ጊዜ የምግብ ዋስትና እጦት በከፍተኛ ሁኔታ ከተጋረጠባቸው ሀገራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡