ለሰሜን ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ ካልቀረበ ህይወታቸው ከባድ ይሆናል ሲል ተመድ አሳሰበ
ከሰኔ እስከ መስከረም ያለው የመኸር ወቅት ኢትዮጵያ ከ85 እስከ 95 በመቶ የምግብ ሰብል የምታመርትበት ወቅት ነው
ተመድ የሰሜን ኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በመኸር ወቅት አስቸኳይ ዘርና ማዳባሪያ ያስፈልገዋል አለ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ)፤ በግጭት በተጎዳው ሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከዋናው የዝናብ ወቅት አስቀድሞ ዘር እና ማዳበሪያ ሊቀርብላቸው ይገባል ሲል አሳሰበ።
“የመኸር ወቅት (የኢትዮጵያ ዋና የዝናብ ወቅት) ለመደገፍ በግጭት በተጎዳው ሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘሮች እና ማዳበሪያዎች በአስቸኳይ ሊቀርብላቸው ይገባል” ብሏል ኦቻ በወቅታዊ መግለጫው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች የሚፈለገውን እርዳታ ለማሳደግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ቢሆንም፤ የሰሜን ኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ አሁንም እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም ገልጿል።
የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) "ዘር እና ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች የመኸር ወቅት ሳይደርስ በወቅቱ ካልቀረበ፤ በግጭቱ የተጎዱ ማህበረሰቦች ውስጥ ያለው የምግብና አልሚ ምግብ ዋስትና የበለጠ ተጽእኖ ይኖረዋል " ሲልም አስጠንቅቋል።
ከሰኔ እስከ መስከረም ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው ዋናው የኢትዮጵያ የዝናብ ወቅት ከ85 በመቶ እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የምግብ ሰብል ለማምረት አስተዋጽኦ እንዳለው የመንግስት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኦቻ ፤ ዘር እና ማዳበሪያ በአስቸኳይ ማቅረብ ካልተቻለ በግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለስስተኛ ተከታታይ ጊዜ ደካማ የግብርና ወቅት መከሰቱ አይቀሬ ይሆናል "ይህም በአከባቢው ሚኖሩ ማህበረሰቦች ህይወት እና ኑሮ ከባድ ያደርገዋል" ሲል አክሏል።
ለትግራይ ክልል ብቻ 60 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ፣ 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተሻሻሉ የሰብል ዘሮች፣ 40 ሺህ ሊትር ጸረ ተባይ እና 34 ሺህ ሊትር ፈንገስ ኬሚካሎች እንዲሁም ከ12 ሚሊየን ያላነሱ የቤት እንስሳት ክትባቶች፣ መድኃኒቶችና ቁሳቁሶች እንደሚስፈልግም የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በአማራ ክልልም እንዲሁ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን አርሶ አደሮች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከ9 ሚሊየን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ጦርነቱን በቅድመ ሁኔታ ለማቆም እና ሰብአዊ ርዳታ ወደ ክልሉ ለማድረስ ከተስማሙ በኋላ የሰብአዊ እርዳታ በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል እየሄደ ቢሆንም ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቂ እንዳልሆነ ይገልጻል።