ሀገራት ዜጎቻቸውን እያስወጡ ያሉት በጋላባት-መተማ በኩል ነው ተብሏል
የተለያዩ ሀገራት በሱዳን ያሉ ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ ድንበር በኩል ማስወጣት ጀምረዋል።
በሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ መካከል የተጀመረው ጦርነት ስምንተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል።
ለኢድ በዓል ተብሎ የሶስት ቀን ተኩስ አቁም ቢደረግም ጦርነቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው ተብሏል።
- የሱዳን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? ስለጦርነቱ ምን ማወቅ ይፈልጋሉ?
- ጠ/ሚ ዐቢይ “በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ እየሰሩ ነው” ያሉ አካላትን አስጠነቀቁ
ይህ በዚህ እንዳለ የተለያዩ ሀገራት በሱዳን የሚገኙ ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ጥረቶች በማድረግ ላይ እንደሚገኙ በሱዳን ያሉ ምንጮች አል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል።
ከካርቱም ዜጎቻቸውን በአየር ትራንስፖርት ለማውጣት ያልተሳካላቸው ሀገራት በየብስ ትራንስፖርት በኢትዮጵያ ድንበር በኩል እያስወጡ መሆኑን አል ዐይን ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።
ሀገራቱ ዜጎቻቸውን በጋላባት-መተማ በኩል በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግ ከዚያም ወደ ሀገራቸው እያጓጓዙ ነው ተብሏል።
ሀገራቱ ዜጎቻቸውን ከሱዳን እያስወጡ ያሉት በካርቱም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በመነጋገር እንደሆነም ተገልጿል።
እስካሁን ሳውዲ አረቢያ 50 የሚሆኑ ዜጎቿን ከሱዳን ያስወጣች ሲሆን ሌሎችም ሀገራት በጥረት ላይ ናቸው ተብሏል።
ሀገራት ዜጎቻቸውን በካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በኩል ለማውጣት ቢሞክሩም በስፍራው ከባድ ውጊያ መቀጠሉን ተከትሎ አለመሳካቱ ተገልጿል።
ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን በያዘው የሱዳን ጦርነት እስካሁን ከ415 በላይ ንጹሀን መገደላቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጻል።