የተመድ የስደተኞች ኤጂንሲ በ136 ሀገራት የሚያደርገውን ድጋፍ አቋረጠ
ኤጂንሲው አገልግሎቱን ያቋረጠው ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ለ90 ቀናት ማገዳቸውን ተከትሎ ነው
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚጠቁመት ዋሽንግተን ለኤጄንሲው በአመት 2.49 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ታደርጋለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለውጭ ሀገራት የሚደረጉ ድጋፎች ለ90 ቀናት እንዲታገዱ መወሰናቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የእርዳታ ኤጀንሲዎች ስራቸውን እያቋረጡ ነው፡፡
በ136 ሀገራት ከመኖሪያ ቤታቸው በአስገዳጅ ሁኔታዎች ለተፈናቀሉ 122 ሚሊዮን ሰዎች የህይወት አድን እርዳታ የሚያደረግው የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ሃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ የተለያዩ ወጪ ቅነሳዎች እንዲደረጉ በየአካባቢው ለሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ኢሜል ልከዋል።
ኤጀንሲው የአሜሪካ ድጋፍ ማቋረጥን ተከትሎ ከድንገተኛ ሁኔታዎች አቅርቦት በስተቀር ለ90 ቀናት አዲስ ድጋፎች እንዳይደረጉ፣ የቅጥር እና የኮንትራት ማቋረጥ እንዲሁም ሁሉም አለም አቀፍ የአውሮፕላን ጉዞዎች እንዲቆሙ አዟል፡፡
አዲሱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የእርዳታ ማቋረጡ በዋና መድኃኒቶች ላይ፣ የሕክምና አገልግሎት፣ ምግብ እና መሰረታዊ የዕርዳታ አቅርቦቶች ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ተናግረው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የእርዳታ ማቋረጡ በአለም ዙሪያ በሚገኙ የሰብአዊ እርዳታዎች ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ የተለያዩ ድጋፎች እንዲቋረጡ እና እንዲቀነሱ እያደረገ እንደሚገኝ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ሃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ “አብዛኞቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና ሌሎች አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በእርዳታው መቋረጥ ምክንያት ተስተጓጉለዋል፤ በአለም ዙሪያ የሰብአዊ እርዳታ ፕሮግራሞች ሰራተኞችን ለማባረር እና ስራቸውን በጊዜያዊነት ለማቆማ ተገደዋል” ነው ያሉት።
ሀላፊው ለሁሉም ቅርንጫፍ ቢሮዎቻቸው በኢሜል ባለኩት መልዕክት “ይህ የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ በስደተኞች፣ በተፈናቀሉ ሰዎች እና በስራችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወጪዎችን በመቀነስ በጥንቃቄ መቀጠል አለብን” ብለዋል።
የ2024 የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የተመድ የስደተኞች ኤጄንሲ አንድ አምስተኛ ወጪ (2.49ቢሊየን ዶላር) የሚሸፈነው አሜሪካ በምታደርገው ድጋፍ ነው፡፡
የትራምፕ የገንዘብ ድጋፍ እገዳ ተግባራዊ የሆነው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ የአለም ህዝብ በጦርነት እና ግጭት በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ስደተኛ ሆኖ በሚኖርበት ጊዜ መሆኑን ተከትሎ ችግሮች እንዳይባባሱ ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል፡፡
ለረጅም ጊዜ የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ ከአሜሪካውያን ፍላጎት እና እሴቶች ጋር የማይጣጣም በሀገሮች ውስጥ እና በሀገሮች መካከል ሰላማዊ ግንኙነቶችን የሚያቃረኑ ጉዳዮችን ለማሰፈጸሚያነት ውሏል ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ ተናግረዋል ።