ተመድ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚውል የ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል ተገባለት
ድርጅቱ በኒውዮርክ ባካሄደው ገቢ ማሰባሰቢያ በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ከጠየቀው ሲሶው ብቻ ነው ቃል የተገባለት
በሶስቱ ሀገራት 32 ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ ይፈልጋሉ ተብሏል
የተባበሩት አምንግስታት ድርጅት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ድጋፍ ለማሰበሰብ በጠራዉ ጉባኤ የ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል ተገባለት።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ በችግር ውስጥ ለሚገኙ 32 ሚሊየን ዜጎች ለመድረስ የ7 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቁ ይታወሳል።
ትናንት በኒውዮርክ በተካሄደው ድጋፍ የማሰባሰብ ዝግጅት ግን የ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ነው ቃል የተገባለት።
ከትናንቱ የድጋፍ ቃል በፊትም ቢሆን ኢትዮጵያ 22 በመቶ፣ ኬንያ 21 በመቶ እንዲሁም ሶማሊያ 25 በመቶ ብቻ የድጋፍ ገንዘብ እንዳገኙ በመግለጽ ድርጅቱ ቅሬታውን አሰምቷል።
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “የአፍሪካ ቀንድ ነዋሪዎች ምንም ባላዋጡበት የአየር ንብረት ቀውስ ዋጋ እየከፈሉ ነው” ብለዋል።
በቀጠናው ክብረወሰን የያዘ ረጅም የድርቅ አደጋ መከሰቱንና ይህንኑ አደጋና ጦርነትና ግጭትን ሽሽት ሚሊየኖች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አብራርተዋል ዋና ጸሃፊው።
ባለፈው አመት በሶማሊያ ብቻ ከ40 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን በድርቅ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉንም አስታውሰዋል።
ከ32 ሚሊየን በላይ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በፍጥነት ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ ካልተቻለም “የከፋ ቀውስ” ይከሰታል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።
የመንግስታቱ ድርጅት ከዚህ ቀደምም ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርሱና ቃል የገቡትን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ሲወተውት መቆየቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
በኒውዮርኩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አሜሪካ ከፍተኛውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች፤ 524 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል በመግባት። ይህም በ2023 ለሀገራቱ ያደረገችውን ድጋፍ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ያደርሰዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ “የሁላችንም ትብብር የሚጠይቅ አለማቀፍ ችግር ነው” ያሉትን የአየር ንብረት ለውጥ ለመግታትና የሰብአዊ ድጋፎችን ለማቅረብ መተባበር ይኖርብናል ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን 185 ሚሊየን ዶላር፣ ጀርመን 163 ሚሊየን ዶላር፣ ብሪታንያ እና ኔዘርላንድስ ደግሞ 120 እና 92 ሚሊየን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል።