የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ አጸደቀ
እቅዱ በ14 ድጋፍ እና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ ተግባረዊ እንዲሆን ድጋፍ አግኝቷል
የምክር ቤቱን ድጋፍ እንደሚቀበለው ያስታወቀው ሀማስ በቅድመ ስምምነት ጉዳዮች ዙሪያ ከእስራኤል ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ አጸደቀ።
አሜሪካ በእስራኤል እና በሀማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ጦርነቱ በሚቆምበት ዙሪያ ሁለቱ አከላት እንዲነጋገሩ ባቀረበችው የተኩስ አቁም እቅድ ወይም ምክረ ሀሳብ ላይ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽ ሰጥቷል፡፡
15 አባላት ባሉት ምክር ቤት ትላንት ማምሻውን በተደረገ የድምጽ አሰጣጥ ምክረ ሀሳቡ የ14 ሀገራትን ድጋፍ ሲያገኝ ሩሲያ ድምጸ ተአቅቦ አድርጋለች፡፡
ምክር ቤቱ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመርያ ግዜ ድጋፍ በሰጠው የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ ሁለቱ ወገኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት ስምምነቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጠይቋል፡፡
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊናዳ ቶማስ ውሳኔ ሀሳቡን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት “ዛሬ ድምጽ የምንሰጠው ሰላምን ለማንበር ሲሉ ንግግር የጀመሩ ሲሆን ሀማስ የስምምነት ሀሳቡን የሚቀበል ከሆነ ጦርነቱ በአንድ ቀን ይቆማል” ብለዋል፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈውን የውሳኔ ሀሳብ እንደሚቀበለው ይፋ ያደረገው ሃማስ ስምምነቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ዝርዝር ጉዳዮች ዙርያ ከእስራኤል ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በተመድ የእስራኤል ከፍተኛ ዲፕሎማት ሻፒር ቤን ናፍታሊ “እስራኤል በጦርነቱ ዙርያ ያላት አቋም የማይዋዥቅ ነው፤ ሁሉንም ታጋቾች እስከምናስመልስ እና የሀማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስከሚንኮታኮት ድረስ ጦርነቱን እንቀጥላለን” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
አክለውም እስራኤል ሀማስ ለጊዜ መግዣነት በሚጠቀማቸው ትርጉም አልባ ድርድሮች ላይ በመሳተፍ ጊዜዋን አታጠፋም ነው ያሉት፡፡
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በበኩላቸው እስራኤል ስምምነቱን ለመቀበል ዝግጁ መሆናን ተናግረዋል፡፡
በድምጽ አሰጣጡ ላይ ድምጽ ተአቅቦ ያደረገችው ሩሲያ አምባሳደር ቫስሊ ንቤንዚያ በጦርነቱ መቆም ላይ ሩሲያ የሀሳብ ልዩነት እንደሌላት ገልጸው የአሜሪካ የስምምነት ሀሳብ ግን ያልጠራ አካሄድን የሚከተል ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡
“አሜሪካ ሀማስ ስምምነቱን እንዲቀበል ጫና እያደረገች ትገኛለች፤ በዚህ በኩል ግን እስራኤል አሁንም በጦርነቱ እገፋለሁ እያለች ባለችበት ሁኔታ በአንድ ወገን ላይ ብቻ ተጽእኖ ለማሳደር የተዘጋጀ ረቂቅ በመሆኑ ሩሲያ ይህን ስምምነት ከመደገፍ ታቅባለች” ብለዋል፡፡
በተመድ የአልጄሪያ አምባሳደር የስምምነቱ ነጥቦች ያላጠሩት በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ለዲፕሎማሲያዊ አማራጮች እድል ለመሰጠት በሚል ምክረ ሀሳቡን ደገፈናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ለ8ተኛ ግዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያቀኑት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቀጠናው ሀገራት መሪዎች ጋር እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ተገናኝተው የስምምነቱን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ ውይይቶችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር የተገኛኙት ብሊንከን በውይይታቸው ወቅት ኔታንያሁ ሀማስን ከማጥፋት ወደ ኋላ እንደማይመለሱ ስለመናገራቸው ሮይተርስ አስነብቧል፡፡
አሜሪካ ያቀረበችው በሶስት ዙር የሚፈጸመው የስምምነት ምክረ ሀሳብ የ6 ወራት ተኩስ አቁም ስምምነት፣ የፍልስጤማዊያን እስረኞች እና የእስራኤላዊያን ታጋቾች ልውውጥ እንዲሁም የእስራኤል ጦር በርካታ ሰዎች ከሚኖሩበት የጋዛ ክፍል ለቆ እንዲወጣ ይጠይቃል፡፡
ሆኖም ሁለቱ ወገኖች ለስምምነቱ ያላቸውን በጎ ድጋፍ ከመግለጽ ባለፈ እስካሁን በይፋ ለመደራደር ፈቃደኝነታቸውን አልገለጹም