አለም ወደ ኑክሌር ጦርነት እየተንደረደረ ነው-ተመድ
የተመድ ዋና ጸኃፊ አለም ኑክሌርን ጨምሮ በሌሎች የጦር መሳርያዎች የበላይነት እሽቅድድም ላይ ተጠምዷል ብለዋል
በ2023 የአለም አቀፍ ወታደራዊ በጀት 2.4 ትሪልዮን ደርሷል
አለም ወደ ኑክሌር ጦርነት እየተንደረደረ መሆኑን የመንግስታቱ ደርጅት(ተመድ) ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናገሩ፡፡
ዋና ጸኃፊው በጦር መሳርያ ቁጥጥር አሶሴሽን አመታዊው ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በ1991 ከሶቭየት ህብረት መፍረስ በኋላ የኑክሌር ጦርነት ስጋት በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል።
ባለፉት አስርት አመታት የሀገራት ወታደራዊ እና የጦር መሳርያ በጀት በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል ያሉት ጉተሬዝ ይህም ምድርን በስለት ጫፍ ላይ እንድትጓዝ ያደረጋትን ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
“ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ የጦር መሳርያዎች ቴክኖሎጂ እያደገ መጥቷል፤ በዚህ ሰአት አለም በሰላም ለመኖር ሳይሆን ለሌላ የአለም ጦርነት እየተዘጋጀ ያለ አስመስሎታል” ተብሏል፡፡
አንቶኒዮ ጉተሬዝ በንግግራቸው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ምእራባዊያን ሀገራት እና ኔቶ ከሩሲያ ጋር የሚገኙበት ሁኔታ የኑክሌር ጦር መሳርያ እንዳያማዝዝ ያሰጋል ያሉ ሲሆን የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነትን ለመቋጨት ለየት ያለ አካሄድን መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በሩስያ እና በዩክሬን ጦርነት የተነሳ በተቀሰቀሰው አለም አቀፋዊ ጂኦፖለቲክሳዊ ትኩሳት የኑክሌር ጦርነት ስጋት ማሻቀቡ ሲገለጽ ይህ ለመጀመርያ ግዜ አይደለም። የአለም ሰላም እና ደህንነት ተመራማሪዎች ይህንኑ ስጋት በተደጋጋሚ አንጸባርቀዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቅርቡ በሴንትፒተርስበርግ በተደረገ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር “የኑክሌር ጦር መሳርያ የምንጠቀመው የሩሲያ ሉአላዊ ግዛት በተጣሰ ግዜ ብቻ ነው አሁን ባለንበት ሁኔታ የዚህ ስጋት የለብንም” ብለዋል፡፡
በሁለቱ ግዙፍ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ታጣቂዎች ዋሽግተን እና ሞስኮ መካከል ያለው የጦር መሳርያ ቅነሳ ስምምነት በመጪው 2026 የሚጠናቀቅ ሲሆን ሁለቱን ሀገራት ጨምሮ ሌሎች የኑክሌር ጦር መሳርያ ባለቤቶች በጦር መሳርያ ቅነሳ ዙርያ የጋራ ስምምነት እንዲያደርጉ የተመድ ዋና ጸኃፊ ጠይቀዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ሌላው በስጋትነት ያነሱት ጉዳይ የወታደራዊ በጀት ማሻቀብን ይመለከታል፡፡
የአለም ወታደራዊ በጀት ባለፉት አመታት በተከታታይነት እየጨመረ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት2.4 ትሪልዮን ዶላር በአለም አቀፍ ደረጃ ለወታደራዊ ወጪ ይበጀታል።
በ2023 የአሜሪካ ወታደራዊ ወጭ የአለምን 40 በመቶ የሚሸፍን ነበር፤ ሀገሪቱ በአመት 916 ቢልዮን ዶላር ወታደራዊ በጀት አላት ይህም የአጠቃላይ ሀገራዊ እድገቷን 3.5 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡
ቻይና 296 ቢሊዮን ዶላር በመበጀት ሁለተኛ ስትሆን ሩሲያ በ109 ቢልዮን በሶስተኛነት ትከተላለች፡፡ የሩሲያ እና ዩክሬን፣ የሀማስ እና ጋዛ ጦርነት እንዲሁም በደቡብ ቻይና ባህር ያለው ውጥረት ለወታደራዊ በጀት ማሻቀብ በምክንያትነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል፡፡
ይህ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ያለው ወታደራዊ ወጪ ለልማት እና ለሀገር ግንባት ከሚወጣው ወጪ የሚስተካከል እንዳንዴም የሚበልጥ እንደሆነ አስረግጠው የተናገሩት አንቶኒዮ ጉተሬዝ መንግስታት ከእርስ በእርስ ሽኩቻ ወጥተው የአየር ንብረት ለውጥ እና ሽብረኝነትን በመሳሰሉ የጋራ ጠላቶች ላይ ያተኩሩ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡