በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 100 ሚሊየን መድረሱን የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ገለፀ
ቁጥሩ እስካሁን በዓለማችን የተመዘገበ ከፍተኛው ነው ተብሎለታል
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ 100 ሚሊየን ቁጥሩ የሚያስደነግጥ ነው ብለዋል
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 100 ሚሊየን መድረሱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ /ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር/ አስታወቀ።
ቁጥሩ በዓለማችን የተመዘገበ ከፍተኛው እና ክብረወሰን የሆነ ሲሆን፤ አንድ መቶኛ የዓለማችን የሀዝብ መጠን የሚሸፍን ወይም በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛት 14 ኛዋ ሀገር ጋር እኩል ቁጥር ያለው እንደማለት ነው ተብሎለታል።
በከፍተኛ መጠን መጨመር የወቅቱ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሚያንማር፣ ናይጄርያ፣ አፍጋኒስታን እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ያሉ ግጭቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርካተቸውም ተመድ አስታውቋል።
አሁናዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ብቻ 8 ሚሊየን ሰዎችን ያፈናቀለ ሲሆን፤ ከተፈናቀሉት 6 ሚሊየን የሚሆኑት ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ናቸው።
ቁጥሩ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንዲሁም በድንበራቸው ውስጥ በግጭት የተፈናቀሉ 53 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች ይገኙበታል።
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ “100 ሚሊየን ለመቀበል የሚከብድ ቁጥር ነው፤ በዛው ልክ የሚያሳስብ እና የሚያስደነግጥ መጠን ነው፤ ይህ በፍፁም መመዝገብ ያልነበረበት ቁጥር ነው” ብለዋል።
የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት /አይ.ኦ.ኤም/ በ2021 ክብረወሰን የሆነ 59.1 ሚሊየን ሰዎች በተለያዩ ሀገራት መፈናቀላቸው ባላፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም።
ቁጥሩ በ2020 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ4 ሚሊየን እንደሚበልጥም ነበር ያስታወቀው።