የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ የወሰደውን የግዲያ እርምጃ ዓለምአቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አወገዘ
ከፍተኛ ኮሚሽነር ባቼሌት “ጁንታው ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሊፈታ ይገባል” ብለዋል
የጁንታው ቃል አቀባይ በበኩላቸው “የተገደሉት የምያንማር እስረኞች 'ብዙ የሞት ፍርድ' የሚገባቸው ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት፤ የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ በአራት የዴሞክራሲ ተሟጋቾችን ላይ የወሰደውን የግዲያ እርምጃ አወገዙ፡፡
ወታደራዊ ጁንታው የሞት ፍርድ እንዳይፈጽም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀረበለትን ተደጋጋሚ ጥሪ ወደ ጎን ብሎ በወሰደው እርማጃ ኩፉኛ ማዘናቸው የገለጹት ኮሚሽነሯ ፤ ጁንታው ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሊፈታ ይገባልም ብለዋል፡፡
"ከዓለም ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች ይቀርቡ የነበረ ቢሆንም፤ ወታደሮቹ ለሰብዓዊነት ምንም ግድ ሳይሰጣቸው እነዚህን ግድያዎች መፈጻቸው አሳዝኖኛል" ብለዋል ባቼሌት በሰጡት መግለጫ።
ይህ ጨካኝ እና አጸፋዊ እርምጃ ወታደሮቹ በህዝቡ ላይ እያካሄዱት ያለውን የጭቆና ዘመቻ ማራዘሚያ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ላይ የወሰደው እርምጃ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቢያስደነግጥም፤ የምያንማር ጁንታ ግን በተቃራኒ እርምጃው ትክክል እንደነበር እየተናገረ ነው፡፡
የጁንታ ቃል አቀባይ ፡ የተገደሉት የምያንማር እስረኞች 'ብዙ የሞት ፍርድ' የሚገባቸው ናቸው ሲሉመደመጣቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የምያንማር ወታደራዊ ጁንታ “የሽብር ድርጊቶችን” ለመፈጸም ተባብረዋል በሚል የከሰሳቸውን አራት የዲሞክራሲ ተሟጋቾችን በሞት መቅጣቱ ይታወሳል፡፡
ከ1980ዎቹ መገባደጃ ወዲህ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገር ምያንማር ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰደችው የግዲያ እርምጃ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ውግዘት አስከትሏል።
በጥር እና በሚያዝያ ወር በዝግ ችሎት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው አራቱ ሰዎች፤ ለቅጣታቸው ምክንያት የሆነው ባለፈው አመት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረውን እና በተቃዋሚዎቹ ላይ ደም አፋሳሽ ርምጃ የወሰደውን ወታደራዊ ጁንታ ለመጣል ሲሞክሩ ከነበሩ ሚሊሻዎች ጋር አብረዋል በሚል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በገዢው ጁንታ ጥላ ስር ሆኖ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው የምያንማር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ድረጊቱን አውግዞታል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጁንታው ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል።
የምያንማር ብሔራዊ አንድነት መንግስት ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ክያው ዛው ቃል አቀባይ "በጣም አዝኛለሁ ... ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጭካኔያቸው ሊቀጣቸው ይገባል" ብለዋል፡፡
ከተገደሉት መካከል የዲሞክራሲ ሰው የሆኑት ክያው ሚን ዩ ( ጂሚ) እና የቀድሞ የህግ ባለሙያና የሂፕ-ሆፕ አርቲስት ፍዮ ዘያ ታው እንደሚገኙበት ግሎባል ኒው ላይት የተሰኘ የምያንማር ጋዜጣ ዘግቧል።
ሌሎቹ የተገደሉት ደግሞ ህላ ማዮ አውንግ እና አውንግ ቱራ ዛው የተባሉ ዴሞክራሲ ተሟጋቾች ናቸው ተብለዋል።
በቀጠናው የመብት ተሟጋች ተቋም የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ኤርዊን ቫን ዴር ቦርግት “እነዚህ ግድያዎች በዘፈቀደ የሰዎችን ህይወት ማሳጣት ሌላው በምያንማር ያለው አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ማሳያዎች ናቸው” ብለዋል።
“አራቱ ሰዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት የተከሰሱት በከፍተኛ ሚስጥራዊ እና ፍትሃዊ ባልሆነ ችሎት ነው፤ በተመሳሳይ ክስ ከተፈረደባቸው ከ100 በላይ ሰዎች በሞት ፍርድ እንደሚቀጡ ስለሚታመን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት” ሲሉም ተደምጠዋል ኮሚሽነሯ።