ተመድ በማዕከላዊ ሶማሊያ በተከሰተው ውጥረት “ከ100 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን ተፈናቅለዋል” አለ
ግጭቱ የተከሰተው በጋልሙዱግ ግዛት አስተዳደር እና “አህሉ ሱና ዋልጃማኣ” ቡዱን መካከል ነው
ከተፈናቃዮቹ መካከልም ከ2 ሺህ በላይ የአካል ጉዳትና የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ይገኙባቸዋል
የሶማሊያ ግዛት በሆነችው የጋልሙዱግ አስተዳደር እና ወታደራዊ ክንፍ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ጉሬል ከተባለች ከተማ ከ100 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን መፈናቀላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
ከአስተዳደሩ ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ወታደራዊ ክንፉ በማእከላዊ ሶማሊያ የሚገኝ “አህሉ ሱና ዋልጃማኣ” የተሰኘ የለዘብተኛ እሰላመዊ ቡዱን ስብስብ ነው ተብለዋል።
አሁን ላይ ውጥረቱ ወደ 28 የገጠር ቀበሌዎች መስፋፋቱንም ነው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት /ኦቻ/ የገለጸው።
ኦቻ ከሞቃዲሾ ባወጣው መግለጫ “ከተፈናቃዮቹ 1 ሺህ 5 ከቤተሰቦቻቸው የተለዩ ታዳጊዎች እንዲሁም 2ሺህ 9 የአካል ጉዳት እና የጤና እክል ያለባቸው ናቸው” ብሏል።
የጋልሙዱግ አስተዳደር ግዛት አስተዳደር ግጭቱን በሀገር ሽማግሌች ለመፍታት ባለመቻሉ “የመንግስት ወታደራዊ ኃይል በ“አህሉ ሱና ዋልጃማኣ” ላይ በወሰደው እርምጃ ከወር በኋላ ጉሬል ከተማን መቆጣጠር ተችሏል” ተብሏል።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት /ኦቻ/ መረጃ እንሚጠቁመው ከሆነ በርካታ ተፈናቃዮች ከቤተሶቦቻቸው ጋር እንዲሁም በየበረሃው ዛፍ ስር ተጠለው ይገኛሉ።
ችግሩን ለማቃለል 7 ሺህ 300 የቤተሰብ ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ የሚያስችሉ ሶስት መጠለያ ጣብያዎች መገንባታቸውንም ነው የተገለጸው።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ቢሆኑም በአካባቢው ካለው የጸጥታ ስጋት አንጻር ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚፈለገው ደረጃ እንዳይንቀሳቀሱ ተገድቧል ሲል ኦቻ ገልጸዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ተፈናቃዮች “ምግብም ሆነ ውሃ(በቦቴ የሚመጣ) የሚያገኙት በቀን አንዴ ብቻ ነው”ም ነው ያለው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት /ኦቻ/::
ኦቻ አክሎም “ከ 700 በላይ ህጻናት ለምግብ እጥረት፣ ተቅማጥ፣አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን እና ለኩፉኝ በሽታ ተጋልጠዋል፡” ብሏል።
26 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን እንዲሁም 9 ሺህ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውንም ነው ኦቻ ያስታወቀው።