በ2023 በኢትዮጵያ አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብ 4 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል - ኦቻ
በሀገሪቱ ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍን የሚሹ መሆናቸውን የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል
ከተረጂዎቹ ውስጥ 4 ነጥብ 6 ሚሊየኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ናቸው
በኢትዮጵያ በገጠሙ ተደራራቢ የሰብአዊ ቀውሶች ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታውቋል።
ኦቻ የ2023 የሰብአዊ ቀውስ ምላሽ እቅዱን ይፋ አድርጓል።
በዚህም በሀገሪቱ አስቸኳይ እርዳታ ለሚፈልጉ ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ 3 ነጥብ 99 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል።
ከ2020 ጀምሮ ከባድ ድርቅ የደጋገማት ኢትዮጵያ ከ13 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ አስቸኳይ ድጋፍ ጠባቂ ሆነውባታል ይላል ሪፖርቱ።
በምስራቃዊ እና ደቡባዊ ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅም የምግብ ዋስትና ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰውና የመጠጥ ውሃ እጥረቱ የጤና ወረርሽኞችን እያስከተለ ስለመሆኑም ጠቁሟል።
በሶማሌ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች እስከመስከረም 2022 ድረስ ከ516 ሺህ በላይ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ነው የተባለው።
በድርቅ በተጠቁ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አካባቢዎች ላይ የሚታዩ ግጭቶችም የሰብአዊ ቀውሱን ይበልጥ እንዳያባብሱት ስጋት መፍጠሩን ነው የኦቻ ሪፖርት ያመላከተው።
በአጭር ጊዜ ልዩነት እየጎበኟት ባሉ የድርቅ እና ጎርፍ አደጋዎች ለችግር የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር በ2023ትም እንዲጨምር እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በሰሜኑ ኢትዮጵያም የፌደራሉ መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ከፈረሙ በኋላ በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች መረጋጋት ቢታይም የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎቱ ግን ከፍ ያለ መሆኑ ተጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት ከ4 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው ተፈናቅለው አስቸኳይ ድጋፍ ጠባቂ ሆነዋል የሚለው ኦቻ፥ በ2023ም ግጭቶችን ማርገብ ካልተቻለ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ክፍ ሊል እንደሚችል ስጋቱን አስፍሯል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከአመት አመት ጭማሪ እያሳየ መሄዱን ሪፖርቱ ያመላክታል።
በመሆኑም ከተፈጥሯዊ አደጋዎች በበለጠ ለሚሊየኖች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን ለማብረድ መስራት እንደሚገባ ነው ኦቻ ያሳሰበው።
በ2023 በኢትዮጵያ 20 ሚሊየን አስቸኳይ ድጋፍ ፈላጊዎችን ለመድረስ የሚያስፈልገውን 3 ነጥብ 99 ቢሊየን ዶላር ለማሟላትም አለምአቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቋል።