ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ ይገባል ተባለ
በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ በአንድ ነባር የህወሓት አባል እና ቃል አቀባይ መገለጹ ይበልጥ ቁርጠኛ እንደሚያደርገውም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል
“በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው እጅግ አሰቃቂ እልቂት መሰረታዊ የሚባሉ ዓለማቀፋዊ ህግጋትን የጣሰ ነው”ም ተብሏል
ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ ይገባል ተባለ
ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፍ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ ህወሓት ባሳለፍነው ሳምንት በሰራዊቱ ላይ የፈጸመውን “የክህደት ጥቃት” ተከትሎ በትግራይ ክልል የተጀመረው ህግን ማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ትናንት አንድ ነባር የህወሓት አባል እና ቃል አቀባይ ቡድኑ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን መናገራቸውን ተከትሎ በቡድኑ ውስጥ አሉ ያላቸውን ወንጀለኞች ለመያዝ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁርጠኛ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡
ሰራዊቱ ይበልጥ እየተጠጋ፣ በቡድኑ ቁጥጥር ስር የነበሩ ቦታዎችን ነጻ እያወጣ እና እየተቆጣጠረ በሚያደርገው ግስጋሴ በቡድኑ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይበልጥ እየተገለጹ ነው ያለ ሲሆን “ቡድኑ በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው እጅግ አሰቃቂ እልቂት መሰረታዊ የሚባሉ ዓለማቀፋዊ ህግጋትን የጣሰ ነው” ብሏል፡፡
ህወሓት የፈጸመውን እንዲህ ዓይነቱን “እጅግ አሰቃቂ ጥቃት” ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያውቀው ብቻም ሳይሆን “እጅጉን አጥብቆ ሊያወግዘው እና ወንጀለኞቹን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት የፌዴራሉን መንግስት ሊደግፍ” እንደሚገባ ነው የገለጸው፡፡
ከተጠያቂነት ለማምለጥ በጁንታው የህወሓት ቡድን የሚደረገውን ሙከራ እናውቃለንም ብሏል፡፡
ሆኖም የተጀመረው ዘመቻ ንጹሃንን ታሳቢ ባደረገ አነስተኛ ጉዳት እንደሚፈጸም የማረጋገጫ ቃል ሰጥቷል፡፡
የዘመቻው ፍጻሜ በማያወላዳ ቁርጠኝነት እንደሚታይም ነው የገለጸው፡፡
እንደ ሉዓላዊ ሃገር ኢትዮጵያ ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የራሷን የህግ የበላይነትን አስከብራ ታሳያለችም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው መከላከያ ሰራዊቱ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ጭምር ሙያዊ ብቃቱን ማሳየቱንም ጠቅሷል ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው፡፡
የዘመቻው ግቦች ተሳክተው ሲጠናቀቁ በክልሉ የተቋቋመው እና በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራው ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳደር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በክልሉ ያሰፍናል የሚል ሙሉ እምነት እንዳለውም አስታውቋል፡፡