ሀገራት ግጭቶችን መቆጣጠር ባለመቻላቸው 114 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል- ተመድ
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የተቋቋመበትን ሰላም እና ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት ሊወጣ አልቻለም ተብሏል
ሱዳን፣ጋዛ፣ ዩክሬን እና ኮንጎ በርካታ ህዝብ ከተፈናቀለባቸው የአለም ክፍሎች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅ የስደተኞች ኮሚሽን ሃላፊ ፍሊፖ ግራንዴ የአለም አቀፍ ተፈናቃዮች ቁጥር 114 ሚልየን መሻገሩን ተናግረዋል፡፡
ዋና ኃላፊው ይህ የሆነው ደግሞ ሀገራት ግጭት እና ጦርነቶችን ማስቆም ባለመቻላቸው ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም የጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሰላም እና ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቋቋመ ቢሆንም ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ሲሉ ነው የኮነኑት፡፡
ምክር ቤቱ በጋዛ፣ ዩክሬን፣ሱዳን፣ኮንጎ እና ማያናማር በመካሄድ ላይ የሚገኙ ግጭቶችን በማስቆም ደረጃ ስልጣኑን በአግባቡ እየተጠቀመ አይደለም ብለዋል ዋና ኃላፊው፡፡
በጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው 5ቱ ሀገራት እርስ በእርስ ባላቸው ፖለቲካዊ ሽኩቻ ሁነኛ መፍትሄ መድረስ እንደተሳናቸው ያነሱት ዋና ኃላፊው ይህ ደግሞ በቀን በመቶዎች የሚሞቱባቸው ጦርነቶች እንዲቀጥሉ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በስም ያልጠቀሷቸው ሀገራት ‘’ካልተገራ’’ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመነጨ ለታጣቂዎች እና ሀገራት የሚያደረጉት ድጋፍ ግጭት እና ጦርነቶች እንዲባባሱ እያደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ታጣቂዎች እና የመንግስታት የጸጥታ ሀይሎች ጭምር አለም አቀፍ ህግን በጣሰ መልኩ በንጹሀን ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡
ጾታዊ ጥቃቶች፣ የትምህርት ቤት እና ጤና ተቋማት ውድመት እንዲሁም የንጹሀን ግድያ በጦርነቶች ውስጥ እንደ ጦር መሳርያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ያሉት ፍሊፖ ግራንዴ አለም አቀፉ ማህበረሰብ አይኑ ስር የሚደረጉ ጦርነቶች እና ጀርባ የሰጣቸው ግጭቶች እንዲቆሙ ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ፡፡
በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ነፍሶችን ለመታደግ ዘግይተናል አሁንም ግን ጦርነት እና ግጭቶችን በማስቆም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሀንን ከስቃይ ለመታደግ አልረፈደም ነው ያሉት ፡፡
በሶርያ ለ13 አመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ 5.6 ሚልየን ሶርያዊያን አሁንም በሊባኖስ እና ጆርዳን ይገኛሉ፡፡
በሱዳን 7ሚልየን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ 2 ሚሊዮን ያክሉ ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፣ በማይናማር 3 ሚልየን ሰዎች በሀገሪቱ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በጎረቤት ሀገራት ተጠልለው እየኖሩ ነው። በጋዛ እና ዩክሬን ያለው ሁኔታም ከዚህ እንደማይለይ የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ሀላፊው ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 114 ሚልየን ሰዎች በግጭት እና ጦርነቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሲሆን በመካሄድ ላይ ያሉ ግጭቶች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ አለማችን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ አይታው የማታውቀው ሰብአዊ ቀውስ ልታስተናግድ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል