ተመድ በኢትዮጵያዊው ጄነራል ከፍያለው ምትክ ናጄሪያዊ ጄነራልን የአብየ ጊዜያዊ የፀጥታ ሃይል አዛዥ አድርጎ ሾመ
በሱዳን ጥያቄ መሰረት በአብየ ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚወጣ ተመድ አስውቆ ነበር

ጄነራሉ ለረዥም ዓመታት በናይጀሪያ ጦር ውስጥ ያገለገሉ ልምድ ያላቸው ወታደራዊ አዛዥ መሆናቸውን ተመድ ገልጿል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ናይጀሪያዊው ሜ/ጄነራል ቤንጃሚን ኦሉፊሚ ሳውየርን የአብየ ጊዜያዊ የፀጥታ ሃይል አዛዥ አድርጎ መሾሙን አስታወቀ፡፡
ድርጀቱ የናይጀሪያው ወታደራዊ አዛዥ ሜ/ጄነራል ቤንጃሚን ኦሉፊሚ ሳውየርን የሾመው ፤እስካሁን ድረስ በአብየ ግዛት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ሲመሩ በነበሩት ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ ተሰማ ምትክ እንደሆነም አስታውቋል፡፡
- በአብየ ግዛት የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የመተካቱ ሂደት በቀጣይ ወር ይጀመራል-ተመድ
- ሱዳን በአብዬ ግዛት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለቆ እንዲወጣ ጠየቀች
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያዊው ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ የአብየ ጊዜያዊ የፀጥታ ሃይል (UNISFA) አዘዥ ሆነው ከተሸሙበት ጊዜ አንስቶ ላሳዩት ትጋት፣ የሰጡት አግልግሎት እና ውጤታማ አመራር ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል፡፡
አዲሱ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሳውየር ለ34 ዓመታት በናይጀርያ ጦር ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ሲያገለግሉ የቆዩና እንደፈረንጆቹ ከ2021 ጀምሮ የናይጄሪያ መከላከያ ሰራዊት የመከላከያ መረጃ ዳይሬክተር ሆነው በማገልግል ላይ የነበሩ ናቸው ተብለዋል፡፡
ጄነራሉ በናይጀርያ ጦር ውስጥ ከነበራቸው ውጤታማ አገልግሎት በተጨማሪ እንደፈረንጆቹ ከ2009 እስከ 2010 ድረስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የላይቤሪያ ተልዕኮ የናይጄሪያ ሻለቃ ጦር አዛዥ ሆነው ግዳጃቸው የተወጡ ናቸው፡፡
ሜ/ጄነራል ሳውየር ከናይጄሪያው ከአህሙድ ቤሎ ዩኒቨርሲቲ ዛሪያ በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደሁም ከህንዱ የማድራስ ዩኒቨርሲቲ በመከላከያ እና በስትራቴጂካዊ ጥናቶች ማስተር ኦፍ አርት (MA) አግኝተዋል።
ጄነራሉ እንግሊዘኛ አቀላጥፈው እንደሚናገሩና በፈረንሳይኛ ቋንቋ የመግባባት ክህሎት ያላቸው እንደሆኑም የተመድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በቅርቡ ተመድ በአብየ ግዛት የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የመተካቱ ሂደት በየካቲት ወር ይጀመራል ማለቱ ይታወሳል፡፡
ላለፉት ገዜያት በአብየ ግዛት የነበረው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከስፍራው እንዲወጣ ሱዳን ጥያቄ ማቅረቧ አይዘነጋም፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በነዳጅ ከበለጸገችው የአብየ ግዛት እንዲወጣ ያቀረበችው ጥያቄ በተባበሩት መንግስታት በኩል ተቀባይነት አግኝቶ የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ይወጣ ያለችው በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል በድንበር ጉዳይ አለመግባባት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል፡፡