የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የስደተኞች እርዳታ ጀመረ
ድርጅቱ ባለፈው ሰኔ ወር በመላው ኢትዮጵያ የምግብ እርታውን በስርቆት ምክንያት አቋርጧል
በኢትዮጵያ በጦርነትና በድርቅ ምክንያት 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ እርዳታ ይሻሉ
የተመድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለሚገኙ 900 ሽህ ገደማ ስደተኞች የምግብ እርዳታውን ዳግም መጀመሩ ተነግሯል።
ድርጅቱ በስርቆት ምክንያት እርዳታውን ለወራት አቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ የደህንነትና የመቆጣጠሪያ ስርዓት ካስተካከለ በኋላ ነው ዳግም ማቅረቡን የጀመረው።
ኢትዮጵያ 850 ሽህ የሚሆኑ ስደተኞች ከሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ታስተናግዳለች።
ሀገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራትም 35 ሽህ የሚሆኑ የሱዳን ስደተኞችን ተቀብላለች።
ድርጅቱ ባለፈው ሰኔ ወር በመላው ኢትዮጵያ የምግብ እርታውን አሜሪካ ባቋረጠች በአንድ ቀን ልዩነት ማቋረጡ የሚታወስ ነው።
ስርቆቱን የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና የክልል መንግስታት አቀነባብረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በ30 ዓመታት ታይቶ አይታወቅም በተባለ ድርቅና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ እርዳታ ይሻሉ።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም እርዳታውን ከማቋረጡ በፊት በኢትዮጵያ ለስድስት ሚሊዮን ሰዎች ምግብ እያቀረብኩ ነበር ብሏል።
የድርጅቱ እርምጃው በኢትዮጵያ መንግስት ትችት የገጠመው ሲሆን፤ ምርመራ እንደሚያደርግም አስታውቆ ነበር።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ በሁሉም የስደተኛ መጠለያዎች ማሻሻያ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ 24ቱም መጋዘኖች በዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደሚተዳደሩ ተናግሯል።