በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው የተመድ ኮሚሽን በሃምሌ ወር አጋማሽ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ አስታወቀ
መርማሪዎቹ ወደ ክልሎች መንቀሳቀስ እንዲችሉ የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉም ተብሏል
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በርካታ የሰብዓዊ ህግ ጥሰቶችን መፈጸማቸው የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን በወርሃ ሃምሌ አጋማሽ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ከኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ ማግኘቱ የየፈረንሳዩ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘግቧል፡፡ ኮሚሽኑ አባል የሆኑት ስቴቨን ራትነር “ ሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ ወደ አዲስ አበባ የመሄድ እቅድ” አለን ብለዋል።
የዚህ ጉዟቸው ዓላማም ወደ ሌሎች ክልሎች “ያልተገደበ” የእንቅስቃሴ ፈቃድ ማግኘት መሆኑን ገልፀዋል።
የኮሚሽኑ አባላት በግንቦት ወር ከኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ካሪ ቤሪ ሙሩንጊ ተናግረዋል።
“ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረብነው አዲስ አበባን የመጎብኘት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል”ም ነው ያሉት ሙሩንጊ ።
ሙሩንጊ “በአዲስ አበባ በሚኖረን ምከክር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደ ተፈጸመባቸው አካባቢዎች መርማሪዎቻችን እንዲገቡ፣ ከጥቃት የተረፉትን እና የጥቃቱ ሰለባዎችን እንዲሁም ምስክሮችን እንዲያገኙ ፈቃድ ይሰጠናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም አክለዋል።
በጄኔቫ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ የሆኑት ዘነበ ከበደ ቆርቾ፣ ኢትዮጵያ ያላት ስጋት ከግምት ውስጥ ከገባ “የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ተግባራዊ መንገዶች አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ “አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች” እንዲሁም መንግስት “ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ የሚቋጭበትን” መንገድ እየፈለገ መሆኑን ገልፀዋል ተወካይዋ።
መቀመጫውን ጄኔቫ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከህዳር 3 ቀን 2020 ጀመሮ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት ስልጣን ያለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ኮሚሽን ፤ እንደፈረንጆቹ ታህሳስ 17 ቀን 2021 ማቋቋሙ መሚታወስ ነው፡፡
በተቋቋመው ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች መርማሪ ቡዱን ውስጥ የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ፣ ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እና በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር የኮሚሽኑ አባል መሾማማቸውም ጭምር የሚታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ውስጥ የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሱዳ ባላፍነው ሰኔ 8 ቀን 2022 ከኮሚሽኑ ስለለቀቁ፤ ምክር ቤቱ ስሪላንካዊቷ ራዲካ ኩማራስዋሚን ማካተቱም አይዘነጋም፡፡
ፋቱ ቤንሱዳ ከአባልነት የተሰናበቱት በዩናይትድ ኪንግደም የጋምቢያ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው በመሾማቸው ምክንያት እንደሆነም ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላለፉት ጥቂት ወራት የደረሰበትን ምርመራ አስመልክቶ እሮብ እለት ለምክር ቤቱ የመጀመሪያ የቃል ሪፖርት ማቅረቡ ተሰምቷል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግና የስደተኛ ህግ ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።