በዓለም ላይ 50 ሚሊዮን ዜጎች አሁንም በባርነት ውስጥ እንደሚኖሩ ተመድ ገለጸ
ከዓለማችን ከ150 ሰዎች ውስጥ አንድ ሰው በግዳጅ ስራ ወይም ትዳር ውስጥ ይኖራል ተብሏል
በዓረብ ሀገራት ከፍተኛ የግዳጅ ስራዎች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እንዳሉ ተመድ ገልጿል
በዓለም ላይ 50 ሚሊዮን ዜጎች አሁንም በባርነት ውስጥ እንደሚኖሩ ተመድ ገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ባወጣው ሪፖርት 50 ሚሊዮን የዓለማችን ዜጎች አሁንም በባርነት ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጿል።
በዓለማችን ከሚኖሩ 150 ሰዎች ውስጥ አንድ ሰው በግዳጅ ስራ ላይ ወይም ጋብቻ ውስጥ እንደሚኖሩ የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል።
ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ወይም አይኤልኦ እና የፍልሰተኞች ድርጅት በጋራ ባወጡት ዓመታዊ ሪፖርት 27 ሚሊዮን ዜጎች በግድ ስራ እንዲሰሩ እየተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 15 ሚሊዮን ያህሉ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው ተብሏል፡፡
ተመድ በፈረንጆቹ 2017 ላይ ተመሳሳይ ሪፖርት ይፋ አድርጎ የነበር ሲሆን አሁን ላይ በባርነት የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
በባርነት ተገደው ከሚሰሩ ዜጎች ውስጥ 22 ሚሊዮኑ በእስያ፣ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በአውሮፓ፣ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮኑ በአፍሪካ፣ እንዲሁም 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በአሜሪካ እና 900 ሺህ ያህሉ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ይኖራሉ ተብሏል፡፡
በዓረብ ሀገራት ከአንድ ሺህ ሰዎች መካከል ስድስቱ ተገደው ስራ የሚሰሩ ሲሆን ይህ አሃዝ በሌሎች አህጉራት ካለው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ደግሞ ተገደው በሴተኛ አዳሪነት እንዲሰማሩ ተደርገዋል ያለው ተመድ በተለይም ስደተኞች የዚህ ድርጊት ሰለባ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ተገደው በጋብቻ ውስጥ እየኖሩ ያሉት ዜጎች ቁጥር አሁን ላይ 22 ሚሊዮን ያህል ናቸው የተባለ ሲሆን ይህ አሃዝ ከአምስት ዓመት በፊት በጥናት ከተረጋገጠው ጋር ሲነጻጸር የ6 ነጥብ 6 ብልጫ ዓለው ተብሏል፡፡
እስያ እና ፓሲፊክ አካባቢዎች ከ14 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተገደው በትዳር ውስጥ ያኖራሉ ያለው ተመድ ቀሪው በአፍሪካ እና አውሮፓ እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡
ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ባለባቸው ሀገራት ውስጥ ከአምስቱ ሰዎች መካከል ሶስቱ በግድ በትዳር ውስጥ እየኖሩ ሲሆን በበለጸጉ ሀገራት ደግሞ 26 በመቶዎቹ ሰዎች በተመሳሳይ የግዳጅ ጋብቻ ውስጥ ያሉ ናቸው ተብሏል፡፡