የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ ዳግም ወታደራዊ ግጭት መፈጠሩ እንዳሳሰበው ገለጸ
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ፤ ሁለቱም ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ ለመሻት የተጀመረውን ድርድር እንዲቀጥሉ አሳስበዋል
ሙሳ ፋኪ፤ “ህብረቱ የሀገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የሚደረግ የፖለቲካ ሂደትን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው” ብለዋል
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኢትዮጵያ ዳግም ወታደራዊ ግጭት መፈጠሩ አሳስቦኛል አሉ፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር በሰጡት መግለጫ ፤ በኢትዮጵያ ዳግም ወታደራዊ ግጭት መከሰቱን የሚያመላክቱ ሪፖርቶችን የአፍሪካ ህብረት በቅርበት እየተከታተለ መሆኑም አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም አጥብቀው የጠየቁት ሊቀ መንበሩ፤ ሁለቱም ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄ ለመሻት የተጀመረውን ድርድር እንዲቀጥሉ ሲሉም አሳስበዋል።
በዚህም መሰረት ፤ሁለቱም ወገኖች ከአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጋር እንዲገናኙ ጥሪ አቅርበዋል ሊቀ መንበሩ፡፡
ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ህብረት የሀገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሂደትን ለመደገፍ ከሁሉም አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑም በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
በጥቅምት 2013 ዓ.ም የተጀመረው ጦርነት ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል።
ከስድስት ወራት በላይ ለሚሆኑ ጊዜያት አልፎ አልፎ ከሚከሰቱ ግጭቶች ባሻገር በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል ይህ ነው የሚባል ከባድ ጦርነት ሳይካሄድ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች ሁለቱ ኃይሎች ጦርነቱን በሰላማዊ ንግግር እንዲቋጩ ግፊት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም ሌሎች ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በመንግስት እና በህወሓት መካከል በአስቸኳይ ድርድር አካሂደው ሰላም እንዲያወርዱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተለይ የአፍሪካ ህብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን በመወከል ለወራት መቀለ እና አዲስ አበባ እየተመላለሱ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው አይዘነጋም።
መንግስት ለድርድሩ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ በአፍሪካ ህብረት መሪነት እንዲካሄድ እንደሚፈልግ የገለጸ ሲሆን የህወሓት ድርድሩን ኬንያ እንድትመራው ይፈለጋሉ።
የፌደራል መንግስቱም ሆነ ህወሓት ግጭቱ በድርድር እንዲፈታ ያላቸውን ፍላጎት ቢገልጹም እስከሁን ይህ የሚባል ለውጥ የለም።
ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ፍላጎት እንዳለቸው ይግለጹ እንጂ፤ እስካሁን ውይይት ስለመጀመሩ ወይም ወደዚያው የሚያመራ ተጨባጭ እርምጃ አልታየም።