አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዩክሬን የተፈጸሙ ጭካኔዎች ላይ ጥልቅ ምርመራ መካሄድ አለበት አሉ
ዋና ጸሃፊው ወንጀለኞች በፍትሃዊ እና ገለልተኛ የፍርድ ሂደቶች ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል
የወቅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ሊቀ መንበር ፈረንሳይ "ያለ ፍትህ ሰላም የለም" ብላለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ የተፈጸመው “ጭካኔዎች” ምርመራ እንዲካሄድ አሳሰቡ።
ዋና ጸሃፊው ይህን ያሉት የሩሲያና አሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በተገኙበት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብት አካል ሪፖርቶች “ በዩክሬን ጦርነት ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ማሰቃየትና ሌሎች በሰላማዊ ሰዎች እና የጦር እስረኞች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸማቸው ያሳያሉ” ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ ተፈጽሟል የተባሉት ጭካኔዎች ላይ ዝርዝር ምርመራ ሊካሄድ ይገባልም ብለዋል፡፡
ጣቶችን ወደ ሩሲያ ሳይቀስሩ "ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እነዚህ ሁሉ ክሶች በጥልቀት መመርመር አለባቸው"ብለዋል ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፡፡
ጉቴሬዝ፤ ወንጀለኞች በፍትሃዊ እና ገለልተኛ የፍርድ ሂደቶች ሊጠየቁ ይገባል እንዲሁም ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ፍትህ የማግኘት፣ የማገገሚያና ካሳ የማግኘት መብት አላቸው ሲሉም አክለዋል፡፡
የወቅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ሊቀ መንበር ፈረንሳይ፤ የዩክሬንን ጉዳይ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደትልቅ አጀንዳ አድርጋ ማንሳቷ ይታወቃል፡፡
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና ወደ ስብሰባው ከመግባታቸው በፊት "ያለ ፍትህ ሰላም የለም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በስብሰባው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለውይይት ያልተቀመጡት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና የአሜሪካ አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን መገኘታቸው የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ በ77ኛ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ሩሲያን የሚዳኝ ልዩ የጦር ፍርድ ቤት እንዲቋቋም፣ የጦር ወንጀል የፈጸሙትም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ ከጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልነት እንድትሰረዝም ጥያቄ ማቅረባቸውም ይታወቃል፡፡