ሞስኮ፤ የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚለውን ውንጀላ “ውሸት” ነው አለች
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ፤ የሩሲያ ኃይሎች በኢዚዮም የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋል
ኢዚዮም በተባለ ስፍራ 450 የሚጠጉ በጅምላ ተቀብረው የነበሩ አስክሬኖች እንደተገኙ መረጃዎች እየወጡ ነው
ሞስኮ፤ የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ካርኪቭ ግዛት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚለውን ውንጀላ “ውሸት” ነው አለች፡፡
የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርምጃ የዩክሬኗ ካርኪቭ ግዛት መልቀቃቸውን ተከትሎ ኢዚዮም በተባለ ስፍራ 450 የሚጠጉ በጅምላ ተቀብረው የነበሩ አስክሬኖች እንደተገኙ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገዋል፡፡
ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ ክሱ "በቡቻ ውስጥ እንደነበረው ተመሳሳይ ነው፤ ‘ውሸት ነው’ እናም በዚህ ተረት ውስጥ ያለውን እውነት እንዲታወቅ እናደርጋለን" ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የሩሲያው ቃል አቀባይ ይህን ይበሉ እንጅ የኪቭ ባለስልጣናት በቦታው የጦር ወንጀል እንደተፈጸመ እንደሚያምኑ ይህንንም ሰንደው ለማስቀመጥ እየሞከሩ እንደሆነ በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በቦታው ላይ የሚገኙ መርማሪዎች በእጃቸው የታሰሩ አስክሬኖችን ጨምሮ በርካታ የማሰቃየት ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ለመኖራቸው አመላካች የሆኑ ማስረጃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጅምላ መቃብሩ ውስጥ አብዛኞቹ ንጹሀን ዜጎች ፣ ሴቶችና ህጻናትም ይገኙበታል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ኃይሎች ፈጽመውታል የተባለው ድርጊት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩልም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ የተወገዘ ሆኗል፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፣ በኢዚዮም ደን መቃብሮች መገኘታቸው “እጅግ አስደንጋጭ ነው” ብለዋል።
ድርጊቱ አስደንጋጭና የሩሲያ ኃይሎች ዩክሬን ውስጥ ከፈጸሟቸው ጭካኔ የተሞሉ ወንጀሎች ጋር የሚመሳሰል ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አሜሪካ የጦር ወንጀል በመሰነድ ድጋፍ መስጠት እንደምትቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው “የተፈጸመውን እጅግ እናወግዛለን” ብለዋል።
በኢዚዮም ተገኘ በተባለው የጅምላ መቃብር “እጅጉን መደንገጡ” የገለጸው ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ነው፡፡
ህብረቱ የተፈጸመውን ድርጊት አጥብቆ እንደሚያወግዝ የገለጹት የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል፤ ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ህግጋቶችን የጣሰ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
"በሩሲያ ኃይሎች የሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን እና የጄኔቫን ስምምነቶችን የጣሰ ነው፤ በአስቸኳይ መቆም አለበት" ብለዋል ጆሴፕ ቦሬል፡፡
አክለውም ፤የአውሮፓ ህብረት በዩክሬን ውስጥ እየተፈጸመ ላለው ወንጀል ሩሲያን ተጠያቂ ለመድረግ የሚደረጉ ሁሉንም ጥረቶችን ይደግፋል ብለዋል፡፡