በኢትዮጵያ የተከሰተውን ኃይማኖታዊ ይዘት ያለውን ግጭት “አስደንጋጭ” ነው ሲል ተመድ ገለጸ
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት “በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ ይደረግ” ሲሉ አሳስቧል
ከሰሞኑ በተፈጠሩ ኃይማኖት አዘል ግጭቶች ቢያንስ 30 ሰዎች ሲሞቱ ከ100 በላይ ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የክርስቲያንና የሙስሊም ግጭት ‘አስደንጋጭ’ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ከሰሞኑ ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው የሚመስሉ ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና ለጉዳት መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው፡፡በዚህም የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
- በጎንደር ከተማ የተቀሰቀውን ግጭት በመቆጣጠር አካባቢውን ለማረጋጋት መቻሉን የአማራ ክልል ገለጸ
- በስልጤ ዞን በቤተክርስቲያናት እና በቤተአምልኮዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ጉባኤው አወገዘ
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት፤ ከሰሞኑ በሙስሊሞችና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች ቢያንስ 30 ሰዎች መሞታቸውና እንዲሁም ከ100 በላይ ግለሰቦች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ገልጿል፡፡
በጎንደር ከተማ ሚያዝያ 18 ቀን በቀብር ስነ ስርዓት ላይ ከመካነ መቃብር ውዝግብ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ከ150 በላይ ሰዎችም ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጹ ይታወሳል።
የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግስት የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት መፍጠራቸውን እና እነዚህን ኃይሎች እንደማይታገሱ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው ከሆነ፤ በጎንደር የተጀመረው ግጭት በተለያዩ ክልሎች ወደሚገኙ ከተሞችና ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በፍጥነት መዛመቱም ኮሚሽነሯ በተቋማቸው ድረ-ገጽ ባሰፈሩት መግለጫ አስታውሷል፡፡
"በጎንደር ሁለት መስጊዶች መቃጠላቸውን እና ሁለቱ መስጊዶች በከፊል መውደማቸውን ተረድቻለሁ"ም ብለዋል ባችሌት።
የጎንደሩን ግጭት ተከትሎ በተሰነዘሩ አጸፋዊ ጥቃቶች “በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ሁለት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑ ግለሰቦች በእሳት ተቃጥለዋል፣ አንድ ግለሰብ ተደብድቦ ተገድሏል፤ እንዲሁም አምስት ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጥለዋል” ሲሉም አክሏል፡፡
በደባርቅ እንዲሁም በአፋር ክልልና ድሬዳዋ ተጨማሪ ሁከቶች መከሰታቸውም ጭምር በመግለጫቸው አስፍሯል፡፡
በደባርቅ ከተማ ሚያዝያ 20 ቀን፤ ሁለት መስጅዶች እንደተቃጠሉ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጹ ይታወሳል።
ከነዚህ ሁከቶች ጋር በተያያዘ ቢያንስ በአራት ከተሞች ከ578 የማያንሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ማስታወቁም በመግለጫቸው አሰፍሯል ኮሚሽነሯ፡፡
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት “በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግና አጥፊዋች ለህግ መቅረብ አለባቸው” ሲሉም አሳስቧል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የፍርድ ሂደታቸውን ያለ አድልዎና የአለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ህግ መሰረት በተከተለ መልኩ ፍትሃዊ እንዲሆንም ጠይቋል።
በሃይማኖቶች መካከል ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከልም “መንግስት ተጎጂ ህበረሰቦችንና ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦችን ትርጉም ባለውና አሳታፊ በሆነ መልኩ ለሁከቶች መፍትሔ መሰጠት አለበት”የሚል መልእክታቸው አስተላልፏል፡፡
በጎንደርና ሌሎች ከተሞች ላይ ከተነሱ ግጭቶች በተጨማሪ ሚያዝያ 24 ቀን በአዲስ አበባም በኢድ- ሰላት ወቅት በተነሳው ግርግር ምክንያት፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ እጅ አላቸው የተባሉ 76 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውያለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡