ተመድ ሰራተኞቹ በደቡባዊ ጋዛ ወደሚገኝ ሆስፒታል በተሽከርካሪ እየሄዱ በነበሩበት ወቅት ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ሰራተኞቹ በደቡባዊ ጋዛ ወደሚገኝ ሆስፒታል በተሽከርካሪ እየሄዱ በነበሩበት ወቅት ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጿል።
ተመድ እንደገለጸው በጥቃቱ አንድ ሰራተኛው ሲገደል ሌላኛው ደግሞ ጉዳት ደርሶበታል።
ሰራተኞቹ በራፋ አቅራቢያ ወደሚገኘው የአውሮፓ ሆስፒታል እየሄዱ ነበር ብሏል ተመድ።
ተመድ ጥቃቱን አድርሷል የሚለውን አካል አልጠቀሰም።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል(አይዲኤፍ) ከተመድ የሴፍቲ እና የሴኩሪቲ ዲፓርትመንት ሁለት ሰራተኞቹ በራፋ አቅራቢያ ሰኞ እለት የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የሚደገልጽ ሪፖርት መቀበሉን አረጋግጧል። አይዲኤፍ ክስተቱ በምርመራ ላይ መሆኑንም ገልጿል።
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቃል አቀባያቸው ፍርሃን ሀቅ በኩል ባወጡት መግለጫ በሰራተኛው ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ሀቅ "የተመድ ዋና ጸኃፊ በተመድ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አውግዘዋል፤ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል" ብለዋል።
በሌላ መግለጫ በጋዛ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ 190 የሚሆኑ የተመድ ሰራተኞች መገደላቸውን ጉተሬዝ ተናግረዋል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው መጠነሰፊ ጥቃት እስካሁን ከ35ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት መግለጻቸው ይታወሳል።