“አሜሪካ በዴሞክራሲ ሽፋን የቻይናን ሉዓላዊነት እየጣሰች ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ ተናግረዋል
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን መጎብኘታቸው ህገ ወጥ ድርጊት ነው ሲሉ ኮንነዋል።
በደቡብ ምስራቅ ኢስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ፤ የታይዋን ጉዳይ በእሳት መጫወት መሆኑን እና በእሳት የሚጫወቱ ደግሞ በእሳቱ መጥፋታቸው አይቀርም ብለዋል።
ቻይናን የሚዳፈሩ ሁሉ ይቀጣሉ ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ ተናግርዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ “አሜሪካ በዴሞክራሲ ሽፋን የቻይናን ሉዓላዊነት እየጣሰች ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ዋንግ ዪ በትናትናው እለት በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካ አፈጉባዔ “ቢሊዮን ጠላቶችን እያፈሩ ነው” እንደሆነ ተናግረዋል።
የቻይናን ዛቻ ወደ ጎን በመተው ትናንት ምሽት ታይዋን ታይፒ የገቡት የአሜሪካ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ፤ ዛሬ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ተመልሰዋል።
ቻይናን ባስቆጣው ጉዟቸው ደስተኛ መሆናቸውን ፔሎሲ ቢገልጹም ዓለም ግን ተጨማሪ ውጊያ እንዳይመጣ ሰግቷል።
ቤጅንግ፤ ታይዋንን ከቻይና ጋር የመቀላቀሉ ሂደት አይቀሬ መሆኑን ገልጻለች።የታይዋን ባለስልጣናት የአሁን ድርጊት ግዛቲቱን ቀውስ ውስጥ ይከታታል ስትል ቻይና አስጠንቅቃለች።